በአፋር ክልል በጦርነት ከተጎዱ የጤና ተቋማት ውስጥ ስራ የጀመሩት ስምንት ብቻ ናቸው

በሀሴት ሀይሉ 

በአፋር ክልል በጦርነት ሳቢያ ውድመት እንዲሁም ዘረፋ ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት መካከል አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ስምንት ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። ስልሳ ዘጠኝ የጤና ተቋማት አሁንም የመልሶ ማቋቋም እንደሚያስፈልጋቸው የጤና ቢሮው ገልጿል።  

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንዳሉት በኢትዮጵያ መንግስት “አሸባሪ” ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ኃይል በአፋር ክልል ያሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ወራቶች 77 ውስጥ የጤና ተቋማት ላይ ውድመት እና ዘረፋ ፈጽሟል። ውድመት እና ዝርፊያ ከተካሄደባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ ሃምሳ አምስቱ የጤና ኬላዎች ሲሆኑ ሃያ አንዱ ደግሞ የጤና ጣቢያዎች ናቸው። 

“በክልሉ ውድመት የደረሰባቸው 55 የጤና ኬላዎች እስካሁን ምንም አይነት  አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም” ያሉት ኃላፊው፤ ይህም የሆነው ቅድሚያ ለጤና ጣቢያዎች በመሰጠቱ መሆኑን ገልጸዋል። ለጤና ጣቢያዎች መልሶ ለማቋቋም ትኩረት የተሰጠው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው እነርሱ ስለሆኑ እንደሆነም አስረድተዋል። 

በአፋር ክልል ከሚገኙ ስድስት ዞኖች መካከል በአራት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ማስተናገድ የሚችሉ ሰባት ጤና ጣቢያዎችን በመለየት የመልሶ ማቋቋም ስራ መሰራቱን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል። 

ከሰባቱ ጤና ጣቢያዎች መካከል አራቱ ስራ የጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ባደረገው ድጋፍ ነው። የከተማይቱ የጤና ቢሮ በለገሳቸው የህክምና መሳሪያዎች፣ መድኃኒቶች፣ የንጽህና እና የጽዳት ቁሳቁሶች ስራ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት ተላላክ፣ ጃራ፣ ደዌ እና ዶርቢሲ የተባሉ ጤና ጣቢያዎች ናቸው። የሀረሪ ክልል በበኩሉ የህክምና ግብአቶችን እና ቁሳቁሶችን በማሟላት የካሳጊታ፣ ሀደለኢላ እና ዳራይቱ ጤና ጣቢያዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ አድርጓል። 

“በአሁኑ ወቅት ስምንት የጤና ጣቢያዎችን መልሶ ማቋቋም አልተቻለም” ያሉት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ፤ ሆኖም ለሌሎች ስድስት የጤና ጣቢያዎችን ስራ ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለመስጠት የተለያዩ አካላት ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል። በአዲስ አበባ የሚገኙት የዘውዲቱ እና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች ውአማ እና ሰሙሮቢ የተባሉ ጤና ጣቢያዎች መልሶ ለማቋቋም ቃላቸውን መስጠታቸውን አቶ ያሲን ተናግረዋል። 

አምሬት ኢትዮጵያ የተባለ ተራድኦ ድርጅት ለሶስት ጤና ጣቢያዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጹን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለአንድ ጤና ጣቢያ ተመሳሳዩን እንደሚያደርግ አስታውቋል ብለዋል። የአዲስ አበባው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የጭፍራ ጤና ጣቢያ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የህክምና ግብአቶችን በሟሟላት ላይ እንደሚገኝም አክለዋል። በመዲናይቱ የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተደረገ ድጋፍ የክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለታካሚዎች አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ተነግሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)