የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች የመጠቆሚያ ጊዜ እንዲራዘም 11 የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች ጠየቁ

በተስፋለም ወልደየስ

አስራ አንድ አገር በቀል የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች፤ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዕጩነት የሚቀርቡ ኮሚሽነሮች የመጠቆሚያ ጊዜ እንዲራዘም ጠየቁ። ድርጅቶቹ የመጨረሻዎቹ ዕጩ ኮሚሽነሮች ተለይተው የሚቀርቡበት መመዘኛ ግልጽነት እንዲኖረውም ጥያቄ አቅርበዋል። 

የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶቹ ይህን ጥያቄያቸውን ያቀረቡት ዛሬ ሐሙስ ጥር 5 በጋራ ባወጡት መግለጫ ነው። ድርጅቶቹ ይህን አቋማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤም፤ የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ እየተቀበለ ላለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት በዛሬው ዕለት አስገብተዋል። 

ደብዳቤውን ካስገቡት እና ጥያቄውን ካቀረቡት ድርጅቶች ውስጥ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል እና ሴታዊት ንቅናቄ ይገኙበታል። የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር፣ ኢስት አፍሪካን ኢኒሺዬቲቭ ፎር ቼንጅ፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፣ ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል እና የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን የተባሉት ድርጅቶችም በጥያቄ አቅራቢዎቹ ዝርዝር ተካትተዋል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያመቻቸው የምክክር ሂደት “ሁሉን አካታች፣ ተአማኒ እና ግልጽ መሆኑን” ለመከታተል እና የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ድርጅቶቹ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ጠቁመዋል። የሂደቱ ግልጽነት “በብዙኃን ዘንድ ለሚኖረው ተአማኒነት እና ቅቡልነት ወሳኝ ሚና አለው” ያሉት ድርጅቶቹ፤ አገራዊ ምክክሩን የሚያመቻቸው ኮሚሽን ተአማኒነት “ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶቹ ለአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በዕጩነት የሚቀርቡ ኮሚሽነሮች ጥቆማ፤  ከህዝብ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሰበሰበ መሆኑ “ሊደነቅ የሚገባው” መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል። ከሶስት ሳምንት በፊት በፓርላማ የጸደቀው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ፤ በኮሚሽኑ የሚያገለግሉ 11 ኮሚሽነሮች የሚመረጡት በሕዝብ፣ በፖለቲካ ድርጅቶች እና በሲቪል ማኅበራት ጠቋሚነት ከሚቀርቡ ዕጩዎች እንደሚሆን ይደነግጋል። 

አገር በቀል የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶቹ የዕጩዎች ጥቆማ ሂደቱን በበጎ መልኩ  በመግለጫቸው ቢያነሱም፤ ለጥቆማ “የተሰጠው ጊዜ ግን አጭር ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመው የኮሚሽነሮች ጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴ የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ መቀበል የጀመረው ታህሳስ 26፤ 2014 ነበር። ለአስር ቀናት የተሰጠው የጥቆማ መቀበያ ጊዜ ቀነ ገደብ፤ በነገው  ዕለት ይጠናቀቃል። 

“የኮሚሽነሮች የጥቆማ ጊዜ ማጠሩ ከመረጃው ተዳራሽነት፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ካለው የመገናኛ ዘዴዎች ውሱንነት፣ ብሎም ለኮሚሽነርነት ብቁ የሆኑ ሰዎችን ለማሰብ ከሚወስደው ጊዜ አንፃር በቂ ጥቆማዎች እንዳይደረጉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮብናል” ያሉት አስራ አንዱ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች፤ የመጠቆሚያ ጊዜው እንዲራዘም ጠይቀዋል። 

ድርጅቶቹ ከዚህ በተጨማሪ ያነሱት ሌላው ጉዳይ ለኮሚሽነርነት ከተጠቆሙት ግለሰቦች ውስጥ በመጨረሻ የሚመረጡት ዕጩዎች የሚለዩበትን መመዘኛ የተመለከተ ነው። “በሕዝብ ከተጠቆሙ ኮሚሽነሮች መካከል የመጨረሻ አስራ አራቱ ዕጩዎች በአፈ ጉባዔው ተለይተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ዕጩዎቹ ተለይተው የሚቀርቡበትን መመዘኛ ሁኔታ በተመለከተ የአሠራር ግልጽነት አለመኖሩን አስተውለናል” ሲሉ ድርጅቶቹ በመግለጫቸው አመልክተዋል። 

“በሕዝብ የተጠቆሙት ዕጩዎች በምን መመዘኛ እንደተመረጡ ለብዙኃን ግልጽ ማድረግ የሚቻልበትን አሠራር መመሥረት ለኮሚሽኑ ተአማኒነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን” ሲሉም አቋማቸውን አንጸባርቀዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግም የዕጩዎች መመዘኛው “ግልጽነት እንዲኖረው” ድርጅቶቹ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚ አዋጅ ኮሚሽነሮች የሚመረጡባቸውን ዘጠኝ መሥፈርቶች በዝርዝር አቅርቧል። ከመስፈርቶቹ መካከል በቀዳሚነት የተቀመጠው፤ ኮሚሽነር ሆኖ የሚሾም ግለሰብ ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ እንዲሆን ነው። ኮሚሽነሮቹ “የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል” ሊሆኑ እንደማይገባ በረቂቅ አዋጁ አስገዳጅ ድንጋጌ ተካትቷል። 

“ሁሉንም ሃይማኖቶች፣ የተለያዩ ብሔሮችን፣ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችን እና ሕዝቦችን በእኩል ዓይን” መመልከት ሌላው በኮሚሽነርነት ለመመረጥ የሚያበቃ  መስፈርት ነው። ለቦታው የሚታጭ ሰው “ለአገራዊ መግባባት ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል” መሆን እንደሚገባውም በመስፈርትነት ተጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)