የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጥቆማ ማቅረቢያ ጊዜ በአንድ ሳምንት ተራዘመ

በነገው ዕለት ጥር 6 ይጠናቀቅ የነበረው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ጥቆማ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት መራዘሙን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ። የጥቆማ ማቅረቢያ ጊዜው የተራዘመው “ህዝቡ ተጨማሪ ዕጩዎችን እንዲጠቁም” መሆኑን ምክር ቤቱ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ ገልጿል። 

ዜጎች “እስካሁን ዕጩ ኮሚሽነሮችን ለመጠቆም ያሳዩት ተነሳሽነትና እያደረጉ ያሉት ተሳትፎ የሚያበረታታ ነው” ያለው ምክር ቤቱ፤  “የአገሪቱን ብዝሃነት ታሳቢ በማድረግና  በተለያዩ ምክንያቶች መጠቆም ላልቻሉ ዜጎች ዕድሉን ለመስጠት” በማሰብ የጥቆማ ጊዜው መራዘሙን በመግለጫው አመልክቷል። 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች የመጠቆሚያ ጊዜ እንዲራዘም 11 የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች በዛሬው ዕለት ጥያቄ አቅርበው ነበር።  አስር ቀናት ብቻ የነበረው የጥቆማ መቀበያ ጊዜ “አጭር ሆኖ አግኝተነዋል” ያሉት ድርጅቶቹ፤ ይህም “ከመረጃው ተደራሽነት፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ካለው የመገናኛ ዘዴዎች ውሱንነት፣ ብሎም ለኮሚሽነርነት ብቁ የሆኑ ሰዎችን ለማሰብ ከሚወስደው ጊዜ አንፃር በቂ ጥቆማዎች እንዳይደረጉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል” የሚል ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ለተወካዮች ምክር ቤት ባስገባው ደብዳቤ ተመሳሳይ የጊዜ ይራዘም ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል። ፓርቲው ኢዜማ የኮሚሽነሮች ጥቆማ ጊዜ እንዲራዘም የጠየቀው በ4 ምክንያቶች ነው። የማህበረሰቡ ወቅታዊ ሁኔታ፣ የመገናኛ ብዙሃን ሚና፣ የኮሚሽነሮች የጥቆማ ሂደት እና ለጥቆማ መቀበያ የተሰጠው ጊዜ በቂ አለመሆን በፓርቲው በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)