የኬንያው “ዴይሌ ኔሽን” ጋዜጣ ዘጋቢ ከሁለት ወር ከ15 ቀናት እስር በኋላ ተፈታ

በሃሚድ አወል

ዕለታዊውን የኬንያ ጋዜጣ “ዴይሊ ኔሽን” ጨምሮ የ“ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ” ለሚያሳትማቸው ጋዜጦች የኢትዮጵያ ዘጋቢ የሆነው ጋዜጠኛ ተስፋአለም ተክሌ ከእስር ተፈታ። ጋዜጠኛው ከ77 ቀናት እስር በኋላ የተፈታው ትላንት ቅዳሜ ጥር 7፤ 2014 ነው። 

በአዲስ አበባ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ የነበረው ጋዜጠኛ ተስፋአለም ከሌሎች 40 እስረኞች ጋር የተለቀቀው ትላንት ከቀኑ 9 ሰዓት አካባቢ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። ጋዜጠኛው ከመፈታቱ በፊት ረፋድ ላይ፤ የፖሊስ ጣቢያው ዋና እና ምክትል አዛዦች “ትፈታላችሁ፤ ዋስ ጥሩ” እንዳሏቸው ገልጿል። 

የተፈታነው “አንድ ሰው እስከ አምስት ለሚደርሱ እስረኞች ዋስ እየሆነ ነበር” የሚለው ተስፋአለም፤ ከእስር ከመለቀቃቸው አስቀድሞ  የሁለት ደቂቃ ገለጻ (orientation) እንደተሰጣቸው አክሏል። የጣቢያው አዛዞች ለእስረኞቹ ባደረጉት በዚሁ ገለጻ “እናንተን የያዝናችሁ ለእናንተው ደህንነት ብለን ነው” ማለታቸውን ጋዜጠኛው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድቷል።    

ተስፋአለም በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመታወጁ ሁለት ቀናት በፊት ጥቅምት 21፤ 2014 ነበር። በወቅቱ እሱን ጨምሮ ስምንት ሰዎች እየተዝናኑ ከነበረበት ቦታ በፖሊስ ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን ገልጿል። 

ጋዜጠኛው የሚሰራበት “ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ” ተስፋአለም በታሰረበት ቀን ባወጣው መግለጫ፤ የጋዜጠኛውን እስር በተመለከተ ለኢትዮጵያ መንግስት አቤቱታ ማቅረቡን ገልጾ ነበር። “ኔሽን ሚዲያ ግሩፕ” ለፍትህ ሚኒስቴር እና በግልባጭ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ “የተስፋአለም ደህንነት እንደሚያሳስበው” ጠቅሶ፤ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋዜጠኛው ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ እንዲያሳውቁ ጠይቆ ነበር።

የጋዜጠኛውን እስር ተከትሎ ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) ባወጣው መግለጫ፤ ተስፋአለም የታሰረው “የኢትዮጵያን መንግስት ዘልፏል”፣ “ከአማጺው የሕወሓት ቡድን ጋርም ግንኙነት አለው” በሚለው ተጠርጥሮ እንደሆነ ማስታወቁ አይዘነጋም። ጋዜጠኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ፖሊስ ተመሳሳይ ምክንያት አቅርቦ ነበር ተብሏል። 

ተስፋአለም እና አብረውት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት በፖሊስ ከተያዙ ሁለት ቀናት በኋላ ጥቅምት 23፤ 2014 ነበር። ፖሊስ ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ያዋላቸው “ገዢውን ፓርቲ የብልግና ስድብ ተሳድበዋል” በሚል ጠርጥሯቸው እንደሆነ በወቅቱ ለፍርድ ቤቱ መግለጹን ጋዜጠኛው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርቷል።

ከታሰሩ ከአራት ቀናት በኋላ በድጋሚ ፍርድ ቤት የቀረቡት እነ ተስፋአለም፤ እያንዳንዳቸውን በአንድ ሺህ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ ተወስኖላቸዋል። ፍርድ ቤቱ ዋስትና ከፈቀደላቸው ስምንት ግለሰቦች ውስጥ፤ ከእርሱ እና እንደ እርሱ የትግራይ ተወላጅ ከሆነ ሌላ ተጠርጣሪ በስተቀር ሌሎቹ መፈታታቸውን ተስፋአለም ይገልጻል።  

በፍርድ ቤት የተጠየቀውን የዋስትና ገንዘብ በቤተሰቦቹ አማካኝነት ክፍያ ተፈጽሞ እንደነበር ጋዜጠኛው ያስረዳል። “አንተን ኮማንድ ፖስቱ ይፈልግሃል ብለው ነው ከእስር ያልፈቱኝ” ሲል ያልተፈታበትንም ምክንያት ያስታውሳል። ጋዜጠኛው ለአራተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት በቀረበበት ባለፈው ታህሳስ 26፤ በተመሳሳይ መልኩ በአንድ ሺህ ብር እንዲፈታ ቢወሰንለትም፤ ከሌሎች እስረኞች ጋር እስከተፈታበት ዕለት ድረስ ለ11 ቀናት በእስር እንዲቆይ መደረጉን አብራርቷል። 

ጋዜጠኛ ተስፋአለም አብዛኛውን የእስር ጊዜውን ያሳለፈው በለሚ ኩራ ቀጠና 72 ፖሊስ ጣቢያ ነበር። አብሮት ከታሰረ ሌላ አንድ ግለሰብ ጋር ለተወሰኑ ጊዜያት ሰሚት ጨርቆስ ኮንዶሚኒየም አካባቢ ወደሚገኝ “ማቆያ ቦታ” ተወስዶ እንደነበር ተስፋአለም ተናግሯል። ይህ የማቆያ ቦታ “ለዶሮ እርባታ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ እና ትልልቅ አዳራሾች ያሉበት ነበር” ሲል ጋዜጠኛው አስታውሷል።

በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች 14 ደርሶ እንደነበር ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር። ድርጅቱ በትላንትናው ዕለት በትዊተር ገጹ ባሰፈረው መልዕክት፤ የጋዜጠኛ ተስፋአለምን መፈታት በበጎ እንደሚመለከተው ገልጾ፤ ይህም በኢትዮጵያ በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን ቁጥር ወደ 11 እንዲቀንስ እንዳደረገው ገልጿል።

ሲፒጄ ሌሎች ጋዜጠኞችም ተፈትተው እንደሆነ ለማረጋገጥ እያጣረ እንደሆነም አስታውቋል። በትላንትናው ዕለት ከእስር የተፈቱ ግለሰቦችን በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ለመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጥያቄዎችን ብናቀርብም ምላሽ ማግኘት ሳንችል ቀርተናል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)