በአማራ እና አፋር ክልል በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ፤ አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ የሚገመት ጉዳት ደርሷል ተባለ

በሃሚድ አወል

በአማራ እና አፋር ክልሎች በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ እስከ 930 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት መድረሱን የየክልሎቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች አስታወቁ። ጉዳቱ የደረሰው በሁለቱ ክልሎች ለወራት ሲካሄድ በቆየው ጦርነት ምክንያት መሆኑን የክልሎቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ገልጸዋል። 

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶቹ ይህን የተናገሩት ዛሬ ሰኞ ጥር 9፤ 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደ ሲምፖዚየም ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተዘጋጀው በዚህ ሲምፖዚየም ከተነሱ አጀንዳዎች ውስጥ “ፍርድ ቤቶች እና የዳኝነት አገልግሎት፤ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች” የሚለው አንዱ ነበር።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን በሲምፖዚየሙ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በጦርነት ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ከ635 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ገልጸዋል። በጦርነቱ በአጠቃላይ 61 ፍርድ ቤቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱት የወረዳ ፍርድ ቤቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አብዬ ካሳሁን፤ በጦርነት ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ከ635 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ገልጸዋል

በአማራ ክልል ከሚገኙ 152 የመጀመሪያ ደረጃ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ጉዳት የደረሰው በሃምሳ ስድስቱ ላይ ነው። አራት ተጨማሪ የከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና አንድ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎትም የጉዳቱ ሰለባ ሆነዋል። ጉዳት የደረሰባቸው እነዚህ ፍርድ ቤቶች የሚገኙት በክልሉ ስር ባሉ ሰባት ዞኖች ውስጥ ነው።

ባለፈው አመት በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች በአጠቃላይ የቀረቡ ጉዳዮች ብዛት 751,738 እንደነበር አቶ አብዬ በዛሬው ንግግራቸው ላይ አስታውሰዋል። ከእነዚህ ጉዳዩች ውስጥ 38 በመቶ የሚሆኑት ቀርበው የነበሩት በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው ፍርድ ቤቶች መሆኑንም አስረድተዋል።

በአማራ ክልል በነበረው ጦርነት ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ያህል አግልግሎት ሲሰጡ የቆዩት በከፊል ነበር። ፍርድ ቤቶቹ ከህዳር 1፤ 2014 ጀምሮ እስከ ታህሳስ 17 ድረስ ሲያስተናግዱ የቆዩት የፍትሐ ብሔር ክርክሮች እንዲሁም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ከክልሉ ዝርዝር የዘመቻ አፈፃፀም መመሪያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ብቻ እንደነበር ይታወሳል። 

ጉዳት የደረሰበት የዋግ ኽምራ ከፍተኛ ፍርድ ቤት | ፎቶ፦ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተስፋፋባቸው ስፍራዎች አንዱ በሆነው በአፋር ክልል በሚገኙ ፍርድ ቤቶችም በተመሳሳይ ሁኔታ “ከፍተኛ ጉዳት” መድረሱ በዛሬው ሲምፖዚየም ላይ ተገልጿል። የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሙሳ አብድሌ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ላይ የደረሰው ጉዳት “ከ230 እስከ 300 ሚሊዮን ብር ይደርሳል” የሚል ግምት መኖሩን ተናግረዋል። 

በክልሉ ሁለት የዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና 15 የመጀመሪያ ደረጃ የወረዳ ፍርድ ቤቶች በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው አቶ ሙሳ አስረድተዋል። “የጉዳት መጠኑ ቢለያይም በፍርድ ቤቶቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ተመሳሳይ ነው” የሚሉት የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት የችሎት ማስቻያ አዳራሾች፣ የዳኞች ቢሮዎች፣ የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶች ላይ ዝርፊያ እና ውድመት እንደተፈጸመባቸው አብራርተዋል። 

በአማራ ክልል በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶች ተመሳሳይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዬ፤ “ከደረሰው ጉዳት ሁሉ የከፋው”  ባላለቁ የፍርድ ቤት ጉዳዮች መዝገቦች ላይ የደረሰው ጉዳት መሆኑን አስረድተዋል። በሁለቱም ክልሎች ጅምር የፍትሃ ብሔር እና የወንጀል መዛግብቶች መቃጠላቸውን፣ መጥፋታቸውን እና ከጥቅም ውጭ መደረጋቸውን ፕሬዝዳንቶቹ ገልጸዋል። 

“ከደረሰው ጉዳት ሁሉ የከፋው” ባላለቁ የፍርድ ቤት ጉዳዮች መዝገቦች ላይ የደረሰው ጉዳት መሆኑን የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ተናግረዋል | ፎቶ፦ የሰሜን ወሎ ዞን ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በመዝገብ መጥፋት ምክንያት ወደ ፊት በባለጉዳዮች መካከል የሚከሰት አለመግባባት “አሳሳቢ” መሆኑን የተናገሩት ፀሐይ መንክር የተባሉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፤ ሁለቱ ክልሎቹ ይህን ችግር ለመፍታት ያሰቡት ነገር ካለ ጠይቀዋል። የክልሎቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በቅድሚያ ጉዳት የደረሰባቸውን መዝገቦች የመለየት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። መጥፋታቸው የተረጋገጡ መዝገቦች የሚገኙበት ሌላ ዕድል ካለ ለማግኘት እንደሚሞከር ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሙሳ፤ መዝገቦችን ከባለ ጉዳዮች እና ከዐቃቤ ህግ ለማግኘት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል። “ይኼ በቂ ነው ብለን አናምንም” ያሉት አቶ ሙሳ፤ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተለዩ ቴክኒኮችን በመጠቀም መዝገቦቹን እንደገና አደራጅቶ የፍትህ ስርዓቱ እንዲቀጥል ያደርጋል ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)