ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ከእስር የሚፈቱ ግለሰቦችን ዝርዝር ያዘጋጀው ዐቃቤ ህግ መሆኑን ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ የህዳሴ ግድብ በሚገኝበት ቦታ እስከተደረገው የሚኒስትሮች ስብሳበ ድረስ ከእስር የሚፈቱ ግለሰቦችን ማንነት እንደማያውቁ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስረኞቹ እንዲፈቱ “አንድም የጠየቃቸው መንግስት” እንደሌለም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት ትላንት እሁድ ጥር 8፤ 2014 በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃምሳ ደቂቃ በወሰደው በዚህ ንግግራቸው የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፤ በቅርቡ ከእስር የተፈቱ እስረኞችን በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ ለተፈጠሩ ጥያቄዎችም ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት የምረቃ ስነስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የሚፈቱ እስረኞችን በተመለከተ “ጉዳዩን እኛም መጀመሪያ ስንሰማው አስደንግጦናል” ማለታቸው አነጋግሮ ነበር። እስረኞችን ለመፍታት የተደረሰውን ውሳኔ “ለኢትዮጵያ የሚበጅ፣ ዘላቂ ጥቅም የሚያግዝ፣ በአውደ ውጊያ የተገኘውን ድል በሰላሙ መድረክ እንዲደገም የሚያደርግ” ሲሉ የገለጹት ሲሉ ገለጹትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ውሳኔውን “እየመረረን የዋጥነው እውነት” ሲሉ ገልጸውትም ነበር። 

ይህ አገላለጻቸው ተጨማሪ ጥያቄ መውለዱን የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገሩን ከስር መሰረቱ በማስረዳት በህዝብ ዘንድ የተፈጠረውን መደናገር ለማጥራት ሞክረዋል። እስረኞችን ለመፍታት ከውሳኔ ላይ የተደረሰው ከወር በፊት እንደነበር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሆኖም የሚፈቱ የእስረኞች ዝርዝር እርሳቸውን ጨምሮ ለካቢኔ አባላት የቀረበው የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ የህዳሴው ግድብ በሚገኝበት ስፍራ በተደረገ የሚኒስትሮች ስብሰባ ወቅት እንደነበር አስረድተዋል።   

“እውነቱን ለመናገር ፖለቲካሊ እስረኞችን ለመፍታት ‘እነዚህን ጉዳዮች እናሳካ ነው’ ያልነው እንጂ፤ እነማን ይፈቱ የሚለውን በቀደም ህዳሴ [ግድብ] የሚኒስትሮች ስብሰባ እስካደረግንበት ቀን ድረስ እኔም አላውቅም። እንፍታ ብለን ወስነናል። ዐቃቤ ህግ ሲያጠና ቆይቶ፤ ዝርዝር አመጣልን። ‘እነ እንትናማ አይቻልም፤ እነ እንትና ይቻላል’ ተጨቃጭቀን የተወሰኑ ሰዎች ላይ ወስነን መጣን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሂደቱ ገለጻ አድርገዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲለቀቁ የተደረጉት 30 ግለሰቦች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 20 ሚሆኑት በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ስር ያሉ ተከሳሾች ነበሩ። በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ አራት ተከሳሾችም በተመሳሳይ መልኩ ከእስር እንዲፈቱ ተደርገዋል። በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መዝገብ ክስ ቀርቦባቸው ከነበሩ ተከሳሾች ውስጥ አቶ ስብሃት ነጋን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች “የጤና እና እድሜ ሁኔታቸውን ከግምት በማስገባት” በሚል ምክንያት ክሳቸው ተቋርጦ መፈታታቸው አይዘነጋም። 

እስረኞችን ለመፍታት ሲወሰን የንግግሩ ማዕከል “ግለሰቦች አልነበሩም” ያሉት አብይ፤ የውይይቱ ማጠንጠኛ “የበጎ ፍቃድ ምልክት (gesture) እና ሆደ ሰፊነት (magnanimity) ያስፈልጋል” የሚል እንደነበር ገልጸዋል። “ሀሳቡ፤ ዝም ብሎ ድርቅ ያለ ነገር አድርገን ሀገራችንን እንዳንጎዳ የሚል ነው” ሲሉም አክለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከውሳኔው ጀርባ “የሌላ ሀገር ግፊት አለ” በሚሉ ለሚቀርቡ አስተያየቶችም በትላንቱ ንግግራቸው ምላሽ ሰጥተዋል። እስረኞቹ እንዲታሰሩም ሆነ እንዲፈቱ ጥያቄ ያቀረበ “አንድም መንግስት” እንደሌለ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “አንድም መንግስት ‘እነዚህ ሰዎች ታስረዋልና ፍታ ብሎ የጠየቀኝ የለም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።  

የእስረኞች ፍቺ ጉዳይ በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ውይይት የተደረገበት ከአንድ ወር በፊት መሆኑን የጠቆሙት አብይ፤ ውሳኔው “እስከ ታች ድረስ” ውይይት የተደረገበት እንጂ “እንግዳ ጉዳይ” እንዳልነበር ገልጸዋል። “ሁሉም ክልል ተወያይቶበታል። አሁን ድንገት ደርሶ ‘ድንገት ሆነብኝ’ የሚለው ተቀባይነት የለውም። ከወር በላይ ተወያይተንበታል። አዲስ ነገር አይደለም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)