የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያን ግጭት በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ተጨባጭ ዕድል መኖሩን ከአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መረዳታቸውን ገለጹ። አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትላንት ረቡዕ ጥር 11፤ 2014 ባወጡት መግለጫ፤ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት በአዲስ አበባ እና በመቐለ ስላደረጉት ጉብኝት መነጋገራቸውን ይፋ አድርገዋል።
ኦባሳንጆ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ደም አፋሳሹን ግጭት ለመፍታት እያደረጉ ስላለው ጥረት ማብራሪያ እንደሰጧቸው የገለጹት ዋና ጸሐፊው፤ “አሁን ግጭቱን በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ተጨባጭ ዕድል እንዳለ ተስፋቸውን ገልጸዋል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከአንድ ሳምንት በፊት ታህሳስ 29 ባወጡት መግለጫ፤ ጦርነቱ “በሰላም እንዲጠናቀቅ እናደርጋለን” ማለታቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው “ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ድሮም ልባችን ክፍት ነበር፤ ወደፊትም የሰላም እጃችን አይታጠፍም” ሲሉ በሀገሪቱ ያለውን ጦርነት በሰላም ለመፍታት ፍላጎት መኖሩን ጠቁመዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ በትላንቱ መግለጫቸው “በኢትዮጵያ እና በቀጠናው በሚሊዮን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ካሳደረ የአንድ አመት በላይ ውጊያ በኋላ ሰላም ለማውረድ የሚታይ ጥረት በመኖሩ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል። ይሁንና ጉተሬዝ “በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተካሄዱ ነው” ያሏቸው “ወታደራዊ ተልዕኮዎች”፤ ለሰላም ሂደቱ ተግዳሮት ሆነው መዝለቃቸውን እና በግጭቱ በሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች መካከል መተማመን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት “እክል” መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ጉተሬዝ “ሰላም ለማውረድ ዋነኛ እርምጃ” በሚል በመግለጫቸው የጠቀሱት “ግጭትን በፍጥነት ማቆም” ነው። የተመድ ዋና ጸሐፊ ሁሉም ወገኖች ይህን እርምጃ ተግባራዊ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ሁሉም ወገኖች በኢትዮጵያ ይካሄዳል ለተባለው ብሔራዊ ውይይት “ቅን እና ቁርጠኛ እንዲሆኑ” አለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግም ዋና ጸሐፊው ጠይቀዋል። ተመድ በኢትዮጵያ የሚደረግ አካታች ብሔራዊ ውይይትን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ጉተሬዝ አክለዋል።
ጉተሬዝ በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት በታላቅ ተስፋ እየተከታተሉ ቢሆንም የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ጉዳይ አሁንም እንደሚያሳስባቸው ግን አልሸሸጉም። “በግጭቱ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ለተቸገሩ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ጥረቶች እንዲደግፉ እና እንዲያመቻቹ” ሲሉ የተመድ ዋና ጸሐፊ ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)