የብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

የብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው። ሚኒስትሯ በኢትዮጵያ ቆይታቸው “ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶችን” ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ አስታውቀዋል።  

የብሪታኒያ ምክር ቤት አባል እና በአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮችን በበላይነት የሚመሩት ቪኪ፤ የአዲስ አበባ ጉዟቸውን ይፋ ያደረጉት ዛሬ ሐሙስ ጥር 12 በተረጋገጠ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ነው። ወደ አሁኑ የኃላፊነት ቦታቸው ከመጡ አራት ወር ያለፋቸው ሚኒስትሯ፤ ወደ ኢትዮጵያ ሲጓዙ የአሁኑ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ገልጸዋል።   

ሚኒስትሯ በአዲስ አበባ ቆይታቸው “ጠቃሚ ውይይቶች” እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። ውይይታቸው ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች መካከል “ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር የሚደረግ ጥረቶችን” የሚመለከተው አንዱ መሆኑን በመልዕክታቸው አስፍረዋል። 

“በመላ አገሪቱ ላለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ያለው ምላሽ” ሌላው ውይይት የሚደረግበት ጉዳይ መሆኑን ቪኪ ፎርድ ጠቁመዋል። “ኢትዮጵያ ከብሪታኒያ ጋር ያላት የልማትና የኢኮኖሚ አጋርነት ለመረጋጋት እና ብልጽግና” የሚለው ርዕሰ ጉዳይ በሶስተኛ ደረጃ ለውይይት የተያዘ ነው።

የ54 አመቷ ወግ አጥባቂ የብሪታኒያ ፖለቲከኛ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው አስቀድመው የተጓዙት ወደ ሌላኛው የምስራቅ አፍሪካ ሀገር ኡጋንዳ ነው። ሚኒስትሯ ከኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋር በትላንትው ዕለት ተገናኝተው ተነጋግረዋል። ውይይቱ በብሪታንያ እና ኡጋንዳ መካከል ስላሉ “የጸጥታ እና የንግድ ጉዳዮች” ላይ ያተኮረ እንደነበር ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ  በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

የብሪታኒያ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከየትኞቹ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ አልገለጹም። ሚኒስትሯ ባለፈው ህዳር ወር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ተፈላሚ ወገኖች “ትርጉም ያለው ውይይት” ሊያደርጉ እንደሚገባ እና ተጨማሪ ደም መፋሰስን የማስቀረት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት መስጠታቸውን ገልጸው ነበር። 

የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትሯ ከዚህ በተጨማሪም ለተቸገሩ እርዳታ ይደርስ ዘንድ መፈቀድ እንዳለበት አቋማቸውን አስታውቀዋል። ቪኪ በዚሁ ውይይታቸው በመላው ኢትዮጵያ እየተከናወነ ነው ባሉት የጅምላ እስር ያላቸውን ስጋትም ገልጸው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)