ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዕጩነት ከሚቀርቡ ኮሚሽነሮች መካከል ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ 20 የሲቪክ ማህበራት ጠየቁ

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን በበላይነት ለመምራት በዕጩነት ከሚቀርቡ 14 ኮሚሽነሮች መካከል ቢያንስ ግማሾቹ ሴቶች እንዲሆኑ 20 የሲቪክ ማህበራት ጠየቁ። ማህበራቱ ትላንት እሁድ ማታ በጋራ ባወጡት መግለጫ ሴት የማህበረሰብ መሪዎች ከመጨረሻዎቹ ዕጩዎች መካከል ሊካተቱ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

ከህዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበራት በሚቀርብ ጥቆማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርቡ 14 ዕጩዎች “የሚመረጡበት መስፈርት ግልጽ” አለመደረጉን የሲቪክ ማህበራቱ በጋራ መግለጫቸው ጠቅሰዋል። የመጨረሻ 14 ዕጩዎች የሚመረጡበት መስፈርት እና ሂደት “ግልጽ እና ተዓማኒነት የተሞላበት እንዲሆን” ማህበራቱ ጠይቀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኮሚሽነርት የታጩ ግለሰቦችን ጥቆማ መቀበል የጀመረው ባለፈው ታህሳስ 26 ነበር።  አስር ቀናት ብቻ የተሰጠው የጥቆማ ማቅረቢያ ጊዜ እንዲራዘም እና የመጨረሻዎቹ ዕጩ ኮሚሽነሮች ተለይተው የሚቀርቡበት መመዘኛ ግልጽነት እንዲኖረው፤ የትላንቱን መግለጫ ካወጡት የሲቪክ ማህበራት ውስጥ የተወሰኑቱ ከሳምንት በፊት ጥያቄ አቅርበው ነበር። 

የተወካዮች ምክር ቤት፤ የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ መቀበያ ጊዜውን በአንድ ሳምንት በማራዘም ለጥያቄው ምላሽ የሰጠ ቢመስልም፤ የመጨረሻዎቹ 14 ግለቦች በምን እንደሚለዩ ግን ማብራሪያ ሳይሰጥ ቀርቷል። አንድ በዕጩነት የሚቀርብ ግለሰብ በምክር ቤቱ የተዘረዘሩ ዘጠኝ መስፈርቶችን መሟላት ይጠበቅበታል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዕጩዎች ጥቆማን መቀበል ከጀመረ በኋላ፤ አንድ ግለሰብ መጠቆም የሚችለው አንድ ዕጩ ብቻ እንደሆነ አስታውቆ ነበር። ኮሚሽነሮችን ለመምረጥ የጠቋሚዎች ብዛት በመስፈርትነት እንደማያገለግል የገለጸው ምክር ቤቱ፤ “አንድን ግለሰብ ደጋግሞ መጠቆም ተቀባይነት እንደሌለው” ጥር 2፤ 2014 ባወጣው ማብራሪያ አሳስቧል።  

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ያቋቋመው አዋጅ በረቂቅ ደረጃ ባለበት ወቅት በተደረገ ውይይት፤ “የጾታ ድርሻ” እንደ አንድ መስፈርት በህግ እንዲካተት ሀሳብ ቀርቦ ነበር። ይህ ሀሳብ ተግባራዊ ሳይሆን እንደቀረ በመግለጫቸው ያስታወሱት ሃያዎቹ የሲቪክ ማህበራት፤ “ዕጩ ኮሚሽነሮች በሚመረጡበት ሂደት የጾታ ድርሻ የመምረጫ መስፈርት እንዲሆን” በይፋ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ማህበራቱ “በአደራ ጭምር” በሰጡት ማሳሰቢያ፤ ከአስራ አራቱ የመጨረሻ ዕጩዎች ግማሹ ወይም ሰባቱ ሴቶች ሊሆኑ እንደሚገባ ጠይቀዋል። በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ 11 ኮሚሽነሮች የሚመረጡት፤ በመጨረሻ ለዕጩነት ከሚቀርቡ 14 ግለሰቦች መካከል እንደሚሆን በማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ተደንግጓል።   

እጩዎችን በማጣራቱ ሂደት የሴቶች ድርጅቶች እና አደረጃጀቶች ተወክለው እንዲሳተፉ፤ ሴት የማህበረሰብ መሪዎች የኮሚሽነሮች ዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲካተቱ በጋራ መግለጫ ያወጡት ሃያዎቹ የሲቪክ ማህበራት አሳስበዋል። የጋራ  መግለጫው አካል ከሆኑት ሲቪክ ማህበራት ውስጥ የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት፣ ሴታዊት ንቅናቄ፣ ትምራን ኢትዮጵያ፣ “ውሜን ካን ዱ ኢት”፣ ምዠዠጎዋ የሴቶች ልማት ማህበር እና “ውሜንስ አላያንስ ፎር ፒስ ኤንድ ሶሺያል ጀስቲስ” የተባሉ የሴቶች ማህበራት ይገኙበታል።  

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል የተባሉት የሲቪክ ማህበራትም በጋራ መግለጫው ዝርዝር ተካትተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)