በፌደራል ደረጃ ያሉ ጠበቆችን በሙሉ በአባልነት የሚያቅፍ ማህበር ተመሰረተ

በሃሚድ አወል

በፌደራል ደረጃ በጥብቅና ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች በቀጥታ አባል የሚሆኑበት የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር ምስረታ ተካሄደ። ማህበሩ የምስረታ እና የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ትላንት እሁድ ጥር 15፤ 2014 ያካሄደ ሲሆን የመጀመሪያውን ፕሬዝዳንቱን እና ምክትል ፕሬዝዳንቱን መርጧል። 

የኢትዮጵያ የፌደራል ጠበቆች ማህበር የተቋቋመው ባለፈው አመት ሐምሌ ወር በጸደቀው የፌደራል ጥብቅና አገልግሎት ፍቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር አዋጅ በሚያዝዘው መሰረት ነው። አዋጁ ከጸናበት ጊዜ ጀምሮ ባለው ስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የማህበሩ የመጀመሪያው ጠቅላላ ጉባኤ በፍትህ ሚኒስቴር መጠራት እንዳለበት በድንጋጌው ላይ ተቀምጧል።

የጠበቆች ማህበሩ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ዋና ጸሃፊ እንዲኖረው ተደርጎ እንደሚደራጅ በአዋጁ ላይ በተደነገገው መሰረት፤ በትላንትናው ጠቅላላ ጉባኤ እነዚህን አመራሮች የመምረጥ ሂደት ተከናውኗል። አንድ ሺህ ገደማ መስራች አባላት በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ፤ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ስንዱ ዓለሙ ናቸው።

ስንዱ ከ15 ዓመታት በላይ ከከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በዳኝነት አገልግለዋል። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት ስንዱ አለሙ፤ የህግ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባልም ነበሩ።

ለሰባት ዓመታት በጥብቅና ሙያ ሲሰሩ የቆዩት አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው ደግሞ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል። በዓለም አቀፍ ህግ የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው አቶ ቴዎድሮስ ወደ ጥብቅና ሙያ ከመምጣታቸው በፊት በቀድሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአሁኑ ፍትህ ሚኒስቴር ለሰባት ዓመታት ያህል ሰርተዋል። 

ትላንት በይፋ የተመሰረተው የጠበቆች ማህበር፤ ከህግ ትምህርት ጥራት ጀምሮ በጥብቅና አስተዳደር ዙሪያ ሰፋ ያለ ተሳትፎ እንዲኖረው ተደርጎ በአዋጅ የተቋቋመ ነው። በአዋጁ መሰረት ማንኛውም የጥብቅና ፈቃድ የተሰጠው ግለሰብ ወይም ድርጅት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቀጥታ የማህበሩ አባል ይሆናል።  

ከዚህ ቀደም ተቋቋመው በነበሩ የጠበቆች ማህበራት አባል መሆን ግዴታ እንዳልነበር ከፍትህ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በኢትዮጵያ ከጠበቆች ጋር የተያያዘ የመጀመሪያው ማህበር የተመሰረተው የዛሬ 57 ዓመት ገደማ ነበር።  ዋነኛ አትኩሮቱን በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ያደረገው የዚህ ማህበር ስያሜ “የጠበቆች በጎ አድራጎት ማህበር” የተሰኘ ነው። 

ይኸው ማህበር በዓመቱ ስያሜውን ወደ “የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር” በመቀየር፤ በወቅቱ ለመሰል ማህበራት ፍቃድ ይሰጥ በነበረው የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በአዲስ መልክ ተመዝግቦ ነበር። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በሌሎች ሀገራት እንዳሉ የጠበቆች ማህበራት ሁሉ “የኢትዮጵያ ባር አሶሲየሽን” የተሰኘ ስያሜ ይዟል። 

ይህ ማህበር በአሁኑ ወቅት “የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር” የሚል መጠሪያ አለው። አሁን የተቋቋመው የፌደራል ጠበቆች ማህበር ከአንጋፋው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር በአደረጃጀት እንዲሁም በተግባር እና ኃላፊነት የተለየ መሆኑን የህግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የወንጀል ፍትህ መምህር የሆኑት ዶ/ር ስሜነህ ኪሮስ “ሁለቱ ማህበሮች መሰረታዊ ልዩነት አላቸው” ይላሉ። አዲሱ የፌደራል ጠበቆች ማህበር “ህጋዊ ሰውነት አለው” የሚሉት ዶ/ር ስሜነህ፤ የማህበሩ ዕውቅና “ከምዝገባ ሳይሆን ከህግ የሚመነጭ መሆኑ” ከአንጋፋው ማህበር ጋር የሚለየው መሆኑን ያብራራሉ።   

ከጠበቆች በተጨማሪ ሌሎች የህግ ባለሙያዎችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር እንደ አዲሱ የጠበቆች ማህበር በአዋጅ የተቋቋመ አይደለም። አንጋፋው ማህበር በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተመዘገበውም እንደ ሙያ ማህበር ነው። 

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር የተመሰረተው በአባላቱ በጎ ፍቃደኝነት ሲሆን ከሙያ ማህበርነት የዘለለ ስልጣን የለውም። አዲሱ የጠበቆች ማህበር ግን በአንጻሩ ከጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፍ በአዋጅ ስልጣን ተሰጥቶታል።  

ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር፤ ከጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥ እና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚመራው የፍትህ ሚኒስቴር ነበር። የፍትህ ሚኒስቴር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አወል ሱልጣን “ከዲስፕሊን ውጭ ያሉት አብዛኛው የጠበቃ ፍቃድ አስተዳደር ሂደቶች ከዚህ በኋላ የሚመሩት፤ በዚሁ ማህበር አማካኝነት ነው” ሲሉ አዲሱ የጠበቆች ማህበር ስለተሰጠው ኃላፊነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

የፌደራል ጠበቆች ማህበር ከዚህ በተጨማሪም፤ የህግ ስልጠናዎችን በበላይነት የመምራት እና የህግ ስልጠናን የሚመለከቱ የአዋጁን ድንጋጌዎች የማስፈጸም ኃላፊነትም ተሰጥቶታል። የህግ ስልጠና የሚሰጡ ተቋማትም እውቅናቸውን የሚያገኙት ከማህበሩ እንደሚሆን በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።

የማህበሩ በዚህ መልክ መመስረት ለጠበቆች እንዲሁም ለፍትህ ስርዓቱ አዎንታዊ አስተዋጽኦዎች እንደሚኖሩት በትላንቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የህግ ባለሙያዎች ተናግረዋል። ላለፉት 18 ዓመታት በጥብቅና ሙያ የተሰማሩት አቶ ዘላለም ክፍሌ ማህበሩ “ጠበቃው ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ዕድል ይሰጠዋል” የሚል አመለካከት አላቸው። 

ከ22 ዓመታት በፊት በወጣው “የፌደራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፈቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ” ላይ ለጠበቆች ፈቃድ የሚሰጠው የፍትህ ሚኒስቴር እንደሆነ መገለጹ አግባብ አልነበረም ባይ ናቸው።  “ፈቃድ የሚሰጠው፣ [ጠበቆችን] በዲስፕሊን የሚከሰው ፍትህ ሚኒስቴር ነው። ግን ጠበቃው የሚከራከረው ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር ነው። ይህ paradox ነው” ሲሉ ፍትህ ሚኒስቴር ተሟጋችም ፍቃድ ሰጪም መሆኑ ትክክል እንዳልነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ላለፉት 13 ዓመታት በጥብቅና ሙያ ላገለገሉት ዶ/ር ስሜነህ ኪሮስ ግን የማህበሩ ፋይዳ ጠበቆች ላይ ብቻ የሚያበቃ አይደለም። የሀገሪቱ የፍትህ ስርዓት በዋናነት የተጎዳው “እንደዚህ አይነት ማህበር ባለመኖሩ ነው” የሚሉት ዶ/ር ስሜነህ፤ አሁን የተቋቋመው የጠበቆች ማህበር “የኢትዮጵያን የህግ ስርዓት አንድ እርምጃ ወደ ፊት ያራምዳል ብዬ አምናለሁ” ሲሉ አቋማቸውን አጋርተዋል።

ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት ማህበራት እንዳይቋቋሙ “የመንግስት ጫና” እንደነበር የሚጠቅሱት የህግ መምህሩ፤ ይህ የመነጨው ደግሞ ማህበራቱ በሚኖራቸው ሚና ምክንያት እንደሆነ ያብራራሉ። “ማህበራቱ ሃሳብን form በማድረግ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ነገሮች ላይ ከፍ ያለ ሚና ስለሚጫወቱ” በተቋቋሙት ላይም ቢሆን መንግስት ስማቸውን የማጠልሸት ስራ ይሰራ እንደነበር ዶ/ር ስሜነህ መለስ ብለው ያስታውሳሉ። 

አንጋፋው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማህበር ያጋጠመው ዕጣ ፈንታ የዶ/ር ስሜነህን አስተያየት ያጠናክራል። እስከ 1997 ድረስ “የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር” በሚል ስያሜ በስራ ላይ የነበረው ማህበሩ፤ በዚያው ዓመት ከተካሄደው ምርጫ ማግስት ወዲህ ግን “በፖለቲካዊ ውሳኔ ከስራ ውጭ መደረጉን” በወቅቱ የማህበሩ አባል የነበሩት አቶ በላይ ከተማ ይናገራሉ። 

“መንግስት ‘ጠበቆች ያልሆኑ የህግ ባለሙያዎችን በአባልነት ይዟል’ በማለት ‘የጠበቆች ማህበር አይደላችሁም’ አለን”

– የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር አባል የነበሩት አቶ በላይ ከተማ ቀደም ሲል የነበረውን የመንግስት ጫና ከገለጹበት የተወሰደ

“መንግስት ‘ጠበቆች ያልሆኑ የህግ ባለሙያዎችን በአባልነት ይዟል’ በማለት ‘የጠበቆች ማህበር አይደላችሁም’ አለን” የሚሉት አቶ በላይ፤ በዚህም ምክንያት በነባሩ ማህበር ምትክ “የኢትዮጵያ ጠበቆች ማህበር” የሚል ሌላ ማህበር እንዲቋቋም መደረጉን ይገልጻሉ። 

ይህን ተከትሎም አንጋፋው የጠበቆች ማህበር ስያሜውን “የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ማህበር” በሚል ለመቀየር መገደዱን ያስረዳሉ። ከ17 ዓመት በፊት ከተፈጸመው የስያሜ መቀየርም ሆነ ከማህበሩ መዳከም ጀርባ የነበረው፤ “ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ደግፋችኋል” የሚል ፖለቲካዊ ምክንያት እንደነበርም አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)