ኦብነግ በኢትዮጵያ ሊካሄድ በታቀደው ብሔራዊ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠ

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) በኢትዮጵያ በሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለመሳተፍ መሟላት አለባቸው ያላቸውን ስድስት ቅድመ ሁኔታዎች አስቀመጠ። ኦብነግ በብሔራዊ ምርጫ ላይ ታይቷል ያለውን አይነት “ጉድለት” በአገራዊ ምክክር ላይ እንዳይደገምም አሳስቧል።

ኦብነግ ቅደመ ሁኔታዎቹን ያስቀመጠው የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰኞ ጥር 9 እስከ ሐሙስ ጥር 12፤ 2014 በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄደው የቆየውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ ነው። የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዚሁ ስብሰባው በሶማሌ ክልል፣ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ መወያየቱ ተገልጿል።

ከስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የውይይት አጀንዳዎች መካከል፤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደውን አገራዊ ምክክር የሚመለከተው አንዱ እንደነበር ኦብነግ በትላንትው ዕለት በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አመልክቷል። ለኢትዮጵያ ጥልቅ እና የረዥም ጊዜ ግጭቶች አዋጭ መፍትሄ ለማበጀት “ከምርጫው በፊት ብሔራዊ ውይይት ማካሄድ ብቸኛው አማራጭ ነው” የሚል አቋም ከነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ ኦብነግ እንደነበር ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አስታውሷል።

ኦብነግ “ተዓማኒ ብሔራዊ ውይይት ከተካሄደ የሶማሌ ክልል ህዝብ የጋራ አተያይ እና አጀንዳ ማዘጋጀት ይገባዋል” የሚል አቋሙን በትላንትናው መግለጫው ቢያንጸባርቅም፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምስረታ ሂደት ላይ ግን የሰላ ተችቱን ሰንዝሯል። “የኮሚሽኑን 11 አባላት ለመምረጥ የተጀመረው ሂደት እና ሂደቱን ለመምራት የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ፤ ጎዶሎ እና ለአንድ ወገን ያደላ ነው” ሲል ተችቷል። ይህ አካሄድም ምክክሩ ከወዲሁ እምነት እንዲታጣበት አድርጓል የሚል አቋሙን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገልጿል።

በኢትዮጵያ የሚካሄድ ብሔራዊ ውይይት “የዓለም አቀፍ መስፈርቶች እና ልምዶች” መለዮዎችን ካሟላ በሂደቱ እንደሚሳተፍ የገለጸው ኦብነግ፤ መሟላት ይገባቸዋል ያላቸውን ቅደመ ሁኔታዎች ዘርዝሯል። ኦብነግ ካቀረባቸው ቅድመ-ሁኔታዎች መካከል “አካታችነት እና እውነተኛ ውክልና” የሚለው ቀዳሚ ነው። ብሔራዊ ውይይቱ “ጠንካራ የድጋፍ መሠረት፣ ተዓማኒ የውክልና ጥያቄ እና ስምምነት የሚደረስባቸውን ጉዳዮች ተግባራዊ ለማድረግ፤ ፖለቲካዊ ፈቃድ እንዲሁም አቅም ያላቸው ተደራዳሪ ፓርቲዎች” የሚካተቱበት መሆን እንዳለበት ኦብነግ ገልጿል።

ኦብነግ በሁለተኛ ደረጃ ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ ብሔራዊ ውይይቱ “በሰፊው ስምምነት የተደረሰበት እና ባለድርሻ አካላት የሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ያለ አድልዖ ተቀባይነት የሚያገኙበት” መሆን አለበት የሚለው ነው። የብሔራዊ ውይይት “አመቻቺዎች ወይም አደራዳሪዎች ተዓማኒ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸው እና በኢትዮጵያ ከሚገኙ ባለድርሻዎች ሁሉ ገለልተኛ” መሆን እንዳለባቸው ግንባሩ በሶስተኛ ቅድመ ሁኔታን አስቀምጧል። 

ግንባሩ የ“አመቻቺዎች ወይም አደራዳሪዎች” ምርጫ “ግልጽ እና አካታች” መሆን እንደሚገባውም አሳስቧል። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር እንደሚለው “በኢትዮጵያ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ አጀንዳ እና በብሔራዊ ውይይቱ ድርሻ ካለው ብሔር የመጣ መሆኑን ማወቅ ጠቃሚ ነው።”

የብሔራዊ ውይይቱ ተሳታፊዎች በጋራ የሚደርሱበት “መግባባት እና ሽምግልናን ጨምሮ የውሳኔ አሰጣጥ ግልጽ እና ሥምምነት የተደረሰበት” መሆን እንደሚኖርበት ኦብነግ በተጨማሪ ቅድመ ሁኔታነት አስቀምጧል። “ስምምነት ላይ የተደረሰባቸው ግልጽ የመምረጫ መስፈርቶች” ሊኖሩ እንደሚገባ ያሳሰበው ኦብነግ፤ በዚህ ሂደት “አድሏዊ የሆኑ ድንጋጌዎች ሊወገዱ” እንደሚገባ አቋሙን አስታውቋል። 

የብሔራዊ ውይይቱ “ዝግጅት፣ አስተዳደር እና የማመቻቸት ሂደት በማንኛውም ቡድንም ሆነ ቡድኖች ለማዘዝ እንዳይሞከር ወይም የቀደመው ምርጫ ጉድለት እንዳይደገም” የኦብነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የብሔራዊ ውይይቱ “ዝግጅት፣ አስተዳደር እና የማመቻቸት ሂደት በማንኛውም ቡድንም ሆነ ቡድኖች ለማዘዝ እንዳይሞከር ወይም የቀደመው ምርጫ ጉድለት እንዳይደገም” የኦብነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እንዲህ አይነቱ እርምጃ ቁልፍ ተከራካሪዎችን ከብሔራዊ ውይይት ሊያስወጣ ወይም ጭርሱን እንዳይሳተፉ በማድረግ ሂደቱን ዋጋ እንደሚያሳጣ ኦብነግ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። 

ኦብነግ በነሐሴ 2013 መጨረሻ እና በ2014 መጀመሪያ በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ መሳተፍ ከጀመረ በኋላ በመጨረሻ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል። “ምርጫው ጉድለት ነበረበት” የሚል አቋም ያለው የኦብነግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታቀደው ብሔራዊ ውይይትም ተመሳሳይ እንከን ሊገጥመው እንደሚችል አስጠንቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)