ኢሰመኮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች “በአፋጣኝ” እንዲለቀቁ ጠየቀ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁ ጥሪ አቀረበ። ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀረበው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነው። 

ኢሰመኮ ዛሬ ረቡዕ ጥር 18፤ 2014 ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡን “አበረታች እርምጃ” ብሎታል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ የሚያደርገውን የውሳኔ ሃሳብ በአፋጣኝ እንደሚያጸድቀው ኮሚሽኑ ተስፋውን ገልጿል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳቡን ከሚያጸድቅበት ቀን ጀምሮ ከእስር የማይለቀቁ ሰዎች ኖረው፣ በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የማይቀርቡ ከሆነ ግን “እስሩ ከህግ ውጭ” እንደሚሆን ኢሰመኮ አስታውቋል። በዚህም የተነሳ የህግ አስከባሪዎች የህግ ማስከበር ተግባራት፤ የሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በመደበኛው ሥርዓት እንዲያከናወኑ አሳስቧል። 

ኢሰመኮ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ “ማንነትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚመስል ሁኔታ” ሰዎች እየታሰሩ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል። ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባወጣቸው መግለጫዎቹ፤ የታሳሪዎች ሁኔታ እንደሚያሳስበው ሲገልጽ ቆይቷል። 

የመብት ተሟጋቹ ተቋም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት ሰሞን ባወጣው መግለጫ፤ ከአዋጁ ጋር በተያያዘ “ህጻናት ልጆች ያሏቸውን እናቶች እና አረጋውያንን ጭምር” በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች የታሰሩባቸው “አንዳንድ ጣቢያዎች እና የማቆያ ስፍራዎች በጣም የተጣበቡ፣ በቂ መጸዳጃ የሌላቸው፤ በቂ አየር እና ብርሃን የማያገኙ” መሆናቸውን መግለጹ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)