የተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራል መንግስት የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2014 በጀት ዓመት ለፌደራል መንግስት የ122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ። ምክር ቤቱ ተጨማሪ በጀቱን በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ዛሬ አርብ ጥር 20፤ 2014 ባካሄደው ሶስተኛ ልዩ ስብሰባው ነው። 

በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ከተገኙት 309 የፓርላማ አባላት መካከል ዘጠኙ የተጨማሪ በጀቱን መፅደቅ ተቃውመውታል። ሌሎች 7 የምክር ቤት አባላት ደግሞ ድምፅ ከመስጠት ተቆጥበዋል። 

ዛሬ ከጸደቀው ተጨማሪ በጀት ውስጥ 106 ቢሊዮን ብር ያህሉ ለመደበኛ ወጪዎች የሚውል ሲሆን 7 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለካፒታል ወጪዎች ተመድቧል። ቀሪው 9 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለወጪ አሸፋፈን እንደሚውል በተጨማሪ በጀት ዝርዝሩ ላይ ተቀምጧል።። 

ለመደበኛ ወጪዎች ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ፤ ለመከላከያ ሚኒስቴር የተመደበው ተጨማሪ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። ለመከላከያ ሚኒስቴር ትጥቅ እና ቀለብ የተመደበው የገንዘብ መጠን 90 ቢሊዮን ብር ነው። 

ከጸደቀው ተጨማሪ በጀት ውስጥ 5 ቢሊዮን ብር የሚሆነው በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚውል ሲሆን ለዕለት እርዳታ ደግሞ 8 ቢሊዮን ብር ተደልድሏል። ለበጀት ሽግሽግ እና ለ2014 በጀት ዓመት መጠባበቂያ ተይዞ የነበረው 11.3 ቢሊዮን ብር ስራ ላይ በመዋሉ፤ በተጨማሪ በጀቱ ውስጥ 8 ቢሊዮን ብር ለመጠባበቂያነት እንዲያዝ ተደርጓል። 

ተጨማሪ በጀቱ ከመጽደቁ በፊት ከፓርላማ አባላት ጥያቄ እና አስተያየቶች ተነስተዋል። አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች፤ ተጨማሪ በጀቱ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ታሳቢ ስላለማድረጉ እና ለመልሶ ግንባታ የተያዘው የገንዘብ መጠን ላይ የሚያጠነጥኑ ነበሩ። 

አብዲከሪም አኪብ የተባሉ የምክር ቤት አባል በሶማሌ እና አፋር ክልል የሚገኙ ሰዎች በድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ “ክልሎቹ ለምን በተጨማሪ በጀቱ አልተካተቱም?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። ዶ/ር ከፈና ኢፋ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል ቦረና እና ጉጂ ዞኖች የተከሰተው ድርቅ በተመሳሳይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ገልጸው፤ “ከሌሎች በጀቶች ተቀንሶ ለእነዚህ አካባቢዎች ቢውል” የሚል ሀሳብ አቅርበዋል።

የአብን ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ “በጦርነቱ ለወደሙ አካባቢዎች የተመደበው በጀት በቂ ነው ብዬ አላስብም” ብለዋል | ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች በጀት ሊያዝላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል። ዶ/ር ደሳለኝ “በጦርነቱ ለወደሙ አካባቢዎች የተመደበው በጀት በቂ ነው ብዬ አላስብም” ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተዋል።

በአፋር እና አማራ ክልሎች በመቶ ቢሊዮን የሚገመት ውድመት ደርሷል የሚሉት እኚሁ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ “ይኼን ያህል ውድመት ለደረሰባቸው አካባቢዎች 5 ቢሊዮን ብር ለመልሶ ግንባታ (reconstruction) በቂ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ የፓርላማ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚኒስትር ዲኤታው በምላሻቸው ቀዳሚ ያደረጉት ለመልሶ ግንባታው የተመደበውን በጀት በተመለከተ ለተነሱት ጥያቄዎች ነው። 

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ከብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ጀምሮ ውይይት መደረጉን የጠቆሙት ዶ/ር እዮብ ሁለት አማራጮች መቅረባቸውን አብራርተዋል። የመጀመሪያው አማራጭ አካባቢዎቹን መልሶ ለመገንባት ራሱን የቻለ አንድ ተቋም መገንባት እና በተቋሙ አማካኝነት ስራውን ማከናወን ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በቶሎ መፍትሔ የሚያመጣ መንገድን መከተል የሚለው ነው።

“ከችግሩ አንገብጋቢነት አንጻር” የፌደራሉ መንግስት ሁለተኛውን አማራጭ መምረጡን ዶ/ር እዮብ ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ከስር ከስር እየጠገኑ ወደ ስራ የማስገባት ስራ መሰራቱን ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

ለመልሶ ግንባታው 5 ቢሊዮን ብር በቂ አለመሆኑን የተናገሩት ዶ/ር እዮብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረኃይል አማካኝነት የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሚኒስትር ዲኤታው “በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች በበጀቱ ሊካተቱ ይገባል” በሚል ከፓርላማ አባላት ለተነሳው ጥያቄ፤ “ለብቻው በአደጋ መከላከል የሚሰራ ስለሆነ ነው እዚህ ጋር አንድ ላይ ያልተካተተው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ የሆነውን የ561.7 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ በጀት ያጸደቀው ከሶስት ወራት በፊት ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ነው። ለ2014 በጀት ዓመት ከተደለደለው ከዚህ ገንዘብ ውስጥ፤ 162.1 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ የተመደበ ነበር። 

ከዓመታዊ በጀቱ ለካፒታል ወጪ የተመደበው 183.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ለክልሎች ለሚሰጥ ድጋፍ ደግሞ 203.9 ቢሊዮን ብር ተይዞ ነበር። ከፍተኛ በጀት ከተመደበላቸው ክልሎች በሁለተኛነት የተቀመጠው የአማራ ክልል ከበጀቱ በብዙ እጥፍ የሚልቅ ገንዘብ በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰበት ማስታወቁ አይዘነጋም።

የአማራ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ፤ ከሶስት ወራት በፊት በክልሉ የደረሰው ጉዳት 279.5 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት ገልጸው ነበር። ይህ የብር መጠን ለ2014 ከተመደበው አጠቃላይ የሀገሪቱ በጀት ግማሽ ያህሉን ይሆናል።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዛሬ በፓርላማ ለጸደቀው ተጨማሪ በጀት መዘጋጀት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት እና የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ታህሳስ ወር በየፊናቸው ባወጧቸው መግለጫዎች አስታውቀው ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተጨማሪ በጀት ጉዳይ ላይ ውይይቱን ያደረገው ከአንድ ወር በፊት ታህሳስ 20፤ 2014 ነበር።

ዛሬ በጸደቀው የተጨማሪ በጀት አዋጅ መግቢያ ላይ “ለተጨማሪ መደበኛና ካፒታል ስራዎች እንዲሁም ለ2014 በጀት ዓመት ከታክስ የሚገኘው ገቢ በመቀነሱ ከሀገር ውስጥ ብድር በመሸፈን የወጪ አሸፋፈንን ለማስተካከል” አዋጁ መደንገጉ ሰፍሯል።

ምክር ቤቱ በዚሁ ስብሰባው፤ በፌደራል መንግስት ተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መምራቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ተጨማሪ በጀቱ የተዘጋጀው፤ “መንግስት በሚሰበስበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ መመለስ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም የተጨማሪ ወጪ ፍላጎትን በበጀት ሽግሽግ ማስተናገድ አዳጋች በመሆኑ” ነው ብሏል።

ሚኒስቴሩ “ተጨማሪ በጀቱ ለሀገር ደህንነት ማስጠበቂያ፣ ለሰብአዊ እርዳታ፣ በጦርነትና ግጭቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ እንዲሁም ለሌሎች አስፈላጊ የመንግስት ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚውል” መሆኑንም በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ዛሬ በጸደቀው የተጨማሪ በጀት አዋጅ መግቢያ ላይ “ለተጨማሪ መደበኛና ካፒታል ስራዎች እንዲሁም ለ2014 በጀት ዓመት ከታክስ የሚገኘው ገቢ በመቀነሱ ከሀገር ውስጥ ብድር በመሸፈን የወጪ አሸፋፈንን ለማስተካከል” አዋጁ መደንገጉ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)