አሜሪካ በኢትዮጵያ በሚገኘው ኤምባሲዋ ለአንድ ዓመት ገደማ ባገለገሉት አምባሳደሯ ምትክ፤ አዲስ ዲፕሎማት መሾሟን አስታወቀች። የአሁኗን የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲን በ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ በጊዜያዊነት የሚተኩት፤ ትሬሲ አን ጃኮብሰን የተባሉ ዲፕሎማት መሆናቸውን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ጥር 23፤ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ አምባሳደር ጊታ ፓሲ ከአምባሳደርነታቸው የሚለቅቁት “ጡረታ ለመውጣት በማቀዳቸው” መሆኑን ይፋ አድርጓል። አምባሳደር ጊታ ፓሲ የጀመሯቸውን ሥራዎች የመቀጠል ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የተገለጸው አዲሷ ተሿሚ፤ በኢትዮጵያ ያለው ግጭት “በአፋጣኝ እንዲቆም” ግፊት የማድረግ የቤት ስራ ተሰጥቷቸዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን አዲሷን ዲፕሎማት የመረጧቸው፤ በኢትዮጵያ ያለው “ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም፣ እየደረሰ ያለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና ረገጣ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲፈቀድ እና በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ግፊት” እንዲያደርጉ እንደሆነ በመስሪያ ቤታቸው የተሰራጨው መረጃ አመልክቷል።
ትሬሲ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መሾማቸው ይፋ እስከሆነበት እስከዛሬው ዕለት ድረስ፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። በኮሶቮ፣ ታጃኪስታን እና ቱርክሜንስታን የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው የሰሩት ትሬሲ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት፤ ከሙሉ አምባሳደርነት ቀጥሎ በኤምባሲው ሁለተኛ ከፍተኛ የስልጣን ቦታ የሆነውን የ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ በመያዝ ነው።
አሜሪካ በአዲስ አበባ ለሚገኘው ኤምባሲዋ በ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ የሚመሩ ዲፕሎማት ስትሾም ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ሀገሪቱ ምርጫ 97ን ተከትሎ የተከሰተውን የፖለቲካ ቀውስ እና የተቃዋሚ ፖርቲ አመራሮች እስር ስትከታተል የነበረው በ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ በነበሩ ዲፕሎማቷ ነበር። በወቅቱ የስራ ጊዜያቸውን ያገባደዱትን አምባሳደር ኦሪሊያ ብራዚልን ተክተው “ቻርዥ ደ አፌር” የነበሩት ቪኪ ሃድልስተን ነበሩ።
ዩናይትድ ስቴትስ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ኤምባሲዋን በበላይነት የሚመሩ ዲፕሎማቶች ስትቀይር የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በትግራይ ክልል ጦርነት እንደተቀሰቀሰ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ቲቦር ናዥ ናቸው። ጦርነቱ አራት ወራት እንዳስቆጠረ፤ አሁን አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ጊታ ፓሲ ተተክተዋል።
ጊታ ፓሲ “ውስብስብ በሆነ ጊዜ” በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ማገልገላቸውን በዛሬው መግለጫው የጠቀሰው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አምባሳደሯ፤ በሀገሪቱ ለነበራቸው ቆይታ አመስግኗቸዋል። አዲሷ ተሿሚ ትሬሲ ወደ አዲስ አበባ የሚያቀኑት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የሻከረው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ሀገራት ግንኙነት የመሻሻል አዝማሚያ ባሳየበት ወቅት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)