የቀድሞ ፓርላማ አባላት በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ በፍርድ ቤት ታዘዙ

በሃሚድ አወል 

የስራ ዘመናቸውን ባለፈው ሰኔ ወር ጨርሰው የተሰናበቱ የፓርላማ አባላት መንግስት ከሰጣቸው ቤት እንዲወጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው፤ የቀድሞ የፓርላማ አባላት ያቀረቡትን የይግባኝ አቤቱታ ውድቅ በማድረግ ነው።

በቁጥር 163 የሆኑት ሁለት ዙር እና ከዚያ በላይ ያገለገሉ የፓርላማ አባላት የይግባኝ አቤቱታውን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያቀረቡት፤ በስር ፍርድ ቤት በመሰረቱት ክስ የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ነበር። በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተመሰረተው ይህ ክስ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤትን የሚመለከት ነው። 

የክሱ መነሻ የሆነው ጉዳይ የተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ለተሰናባች የፓርላማ አባላት በደብዳቤ ያስተላለፈው ትዕዛዝ ነበር። ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ፤ በምክር ቤት አባልነታቸው የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት እስከ ታህሳስ 30፤ 2014 እንዲያስረክቡ በጽህፈት ቤቱ የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በመቃወም፤ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ መስርተዋል። 

ተሰናባች የተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት ክስ፤ በመንግስት ከተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ለመውጣት በአዋጅ የተሰጣቸው መብት መጀመሪያ መከበር እንዳለበት ተሟግተዋል። ከኃላፊነት የተነሱ የሀገርና መንግስት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞችን መብት እና ጥቅም ለመወሰን የወጣው አዋጅ፤ ሁለት የምርጫ ዘመን ወይም ከዚያ በላይ ያገለገሉ የፓርላማ አባላት ከመንግስት ቤት በኪራይ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። 

መንግስት በኪራይ የሚያቀርበው ቤት ባለመኖሩ ምክንያት የኮንዶሚኒየም ቤት ለማግኘት ገንዘብ ሲቆጥቡ መቆየታቸውን የሚናገሩት የፓርላማ አባላቱ፤ “ሰልፍ ተስተካክሎ” የ40/60 መኖሪያ ቤት እንዲሰጣቸው በመንግስት ተወስኖ እንደነበር  ያስታውሳሉ። ሆኖም አባላቱ የተሰጧቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች “ባለመጠናቀቃቸው እና ለመኖሪያነት ምቹ ባለመሆናቸው” ሊገቡባቸው አለመቻላቸውን ያብራራሉ።  

የቀድሞ የፓርላማ አባላት ያቀረቡትን ክስ በመጀመሪያ የመረመረው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ “መልስ መስጠት አይጠበቅበትም” ሲል ከአንድ ወር ገደማ በፊት ወስኖ ነበር። በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኙት ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ፤ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበዋል። 

አቤቱታውን ትላንት ሰኞ ጥር 23፤ 2014 የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔን ማጽናቱን በችሎቱ ላይ የተገኙ አንድ የቀድሞ ፓርላማ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ፍርድ ቤቱ ለውሳኔው መነሻ ያደረገው የመጀመሪያው ምክንያት “የስር ፍርድ ቤትን የሚያሽር ነገር አላገኘሁም” የሚል መሆኑን እኚሁ የቀድሞ የፓርላማ አባል አስረድተዋል። 

ፍርድ ቤቱ በሁለተኛው ምክንያት የጠቀሰው ተሰናባች የፓርላማ አባላት “በመንግስት በተሰጣቸው ቤት ውስጥ ቆይተው የሚከራከሩበት የህግ መሰረት የለም” የሚል መሆኑን ችሎቱን የተከታተሉት ግለሰብ ገልጸዋል። “ጥያቄያችሁ ‘ቤት ይሰጠን’ ወይም ‘በተሰጠን ቤት ውስጥ እንቆይ’ ሳይሆን ‘ቤቶቻችን እስኪጠናቀቁ ድረስ እዚህ እንቆይ’ የሚል ነው። ይህ ጥያቄ የህግ መሰረት የሌለው ስለሆነ አልተቀበልነውም” ሲል ችሎቱ ክሱን ለመሰረቱት የፓርላማ አባላት መግለጹን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት እኚሁ ግለሰብ አክለዋል። 

ተሰናባች የፓርላማ አባላቱ የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ እንደሚሉ፤ ጉዳዩን ለመከታተል በተቋቋመው ኮሚቴ አባል የሆኑ የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የቀድሞ የፓርላማ አባላቱ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ እስኪሉ ድረስ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በኃይል ከሚኖሩበት ቤት እንዳያስወጣቸው በፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ ለማስወጣት በሂደት ላይ መሆናቸውንም አስረድተዋል። 

የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ከ25 ቀናት በፊት በነበረው ውሎው ተመሳሳይ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር። ፍርድ ቤቱ “ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ”፤ ተሰናባች የምክር ቤት አባላቱ በአባልነታቸው ከተሰጣቸው መኖሪያ ቤት እንዲወጡ የተላለፈው ትዕዛዝ ታግዶ እንዲቆይ አዝዞ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)