የተመድ ዋና ጸሀፊ የኦሎምፒክ መንፈስን ታሳቢ በማድረግ በኢትዮጵያ በአፋጣኝ ግጭት እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ወገኖች ለዘመናት የዘለቀውን የኦሎምፒክ መንፈስ ከግምት ውስጥ በማስገባት በአፋጣኝ ግጭት እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ። ዋና ጸሀፊው ጥሪውን ያቀረቡት በመጪው አርብ በቻይና ቤይጂንግ በሚጀመረው የክረምት ኦሎምፒክ ላይ ለመገኘት ወደ ቦታው ከመጓዛቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው። 

ጉተሬዝ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አዳራሽ አጠገብ ዛሬ ማክሰኞ ምሽት በንባብ ባቀረቡት አጭር መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው ባሉት “ግጭት እና ደም መፋሰስ” የሀገሪቱ ህዝቦች ስቃይ መቀጠሉን ተናግረዋል። ለክፍለ ዘመናት በተሻገረው የኦሎምፒክ ባህል መሰረት፤ በየትኛውም አካባቢ የሚገኙ ተፈላሚ ወገኖች ውድድሮቹ እስኪጠናቀቁ ድረስ ግጭት እንዲያቆሙ ጥሪ እንደሚቀርብ ዋና ጸሀፊው አስታውሰዋል። 

በቻይና ቤይጂንግ ለ16 ቀናት የሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ አርብ ጥር 27 ተጀምሮ በየካቲት 13፤ 2014 ይጠናቀቃል። ይህን በመንተራስም በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ወገኖች “ግጭት በፍጥነት እንዲያቆሙ” የተመድ ዋና ጸሀፊ “ብርቱ ተማጽኗቸውን” በዛሬው መግለጫቸው አቅርበዋል። ሁሉም ወገኖች የኦሎምፒክ መንፈስን ተከትለው “ህይወትን እንዲያድኑ፣ ልዩነቶቻቸውን እንዲፈቱ እና ለእውነተኛ ሰላም መንገድ እንዲፈልጉ” ጥሪ አቅርበዋል።     

የግጭቱ መቆም፤ በመላው ኢትዮጵያ ለተቸገሩ ህዝቦች ሰብዓዊ እርዳታን በውጤታማ መልኩ ለማድረስ እንደሚያስችል ጉተሬዝ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። እርምጃው ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን የሚያሳትፈውን እና በጣሙኑ አስፈላጊ የሆነውን “አካታች ውይይት” ለማካሄድ መንገድ የሚጠርግ መሆኑንም አክለዋል።

የተመድ ዋና ጸሀፊ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያን ግጭት በፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ተጨባጭ ዕድል መኖሩን ከአፍሪካ ህብረት ልዩ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መረዳታቸውን ገልጸው ነበር። ከቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጋር በነበራቸው ውይይት፤ ልዩ ልዑኩ በአዲስ አበባ እና በመቐለ ስላደረጉት ጉብኝት መነጋገራቸውን በወቅቱ አስታውቀዋል። 

ይህን ውይይት ተከትሎ ዋና ጸሀፊው ባወጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ እና በቀጠናው በሚሊዮን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ካሳደረ የአንድ አመት በላይ ውጊያ በኋላ ሰላም ለማውረድ የሚታይ ጥረት በመኖሩ ደስተኛ ነኝ” ብለው ነበር። ጉተሬዝ በዚሁ መግለጫቸው “በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተካሄዱ ነው” ያሏቸው “ወታደራዊ ተልዕኮዎች”፤ ለሰላም ሂደቱ ተግዳሮት ሆነው መዝለቃቸውን እና በግጭቱ በሚሳተፉ ሁሉም  ወገኖች መካከል መተማመን ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት “እክል” መሆናቸውን መጠቅሳቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)