በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ህዳር ወር በመንግስት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት በግዳጅ ወደ ጫካ ቦታ ተወስደው፤ ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ በጥይት ተመትተው መገደላቸውን አስታወቀ። የመንግስት ጸጥታና የአካባቢ አስተዳደር ሰዎች ባሉበት የተፈጸመው በተባለው ይህ ግድያ፤ ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ስለመሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች እንዳሉም ኢሰመኮ ገልጿል።
ኢሰመኮ ይህን ያስታወቀው፤ በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያ ላይ ያደረገውን ምርመራ የያዘ ሪፖርት ዛሬ ረቡዕ ጥር 25 ይፋ ሲያደርግ ባወጣው መግለጫ ነው። በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ አርዳ ጅላ በተባለ ቦታ ላይ ህዳር 22፤ 2014 የተፈጸመውን ይህን ጥቃት በተመለከተ ጥቆማ የደረሰው ኢሰመኮ፤ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ በቦታው ላይ በመገኘት ለአምስት ቀናት ምርመራ ማካሄዱን በመግለጫው አመልክቷል።
ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ የተጓዘው የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን የአይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችን፣ የሟች ቤተሰቦችን እና የከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል ተብሏል። የምርመራ ቡድኑ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ48 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ እና የቡድን ውይይት ማድረጉ በምርመራ ሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ቡድኑ ከዚህ በተጨማሪም ተጎጂዎች አንድ ላይ ተሰብስበው ይኖሩበት የነበረን ስፍራ፣ ግድያው ተፈጸመበት የተባለን ቦታ እንዲሁም የሟቾች አስክሬን ያረፈበት የመቃብር ቦታ በመሄድ የመስክ ምልከታ ማድረጉ በሪፖርቱ ሰፍሯል። ኢሰመኮ በምርመራ የደረሰባቸውን ግኝቶች በዘረዘረበት የሪፖርቱ ክፍል ላይ፤ ግድያው በተፈጸመበት ዋዜማ ላይ በፈንታሌ ወረዳ “ለጸጥታ ኦፕሬሽን” ተሰማርተው በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በመነሻነት አስቀምጧል።
በፈንታሌ ወረዳ ሀሮ ቀርሳ ቀበሌ፤ ልዩ ስሙ ኢፍቱ በተባለ ቦታ ላይ ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች ህዳር 21 በተፈጸመው በዚህ ጥቃት፤ 11 ፖሊሶች መገደላቸውን እና ቢያንስ 17 ሌሎች የፖሊስ አባላት መቁሰላቸውን የምርመራ ሪፖርቱ አስታውቋል። ጥቃቱን ያደረሱ ተጠርጣሪዎችን ለመፈለግ የከረዩ ሚችሌ አባገዳዎች እና የጅላ አባላት የመኖሪያ ሰፈር ወደሚገኝበት ጡጢቲ ቀበሌ፣ ልዩ ስሙ ዴዲቲ ካራ ወደ ተባለ ቦታ የሄዱ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች፤ 39 የጅላ አባላትን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን የምርመራ ቡድኑ ከአይን እማኞች ተረድቷል።
ድርጊቱ ሲፈጸም በቦታው የነበሩ አንድ የአይን እማኝ የነበረውን ሁኔታ ለምርመራ ቡድኑ ሲገልጹ “ሁሉንም በቦታው የነበሩ ወንድ የጅላ አባላትን ሰበሰቡ። ቤት የቀሩ ሰዎችንም እንዲወጡ አድርገው አንድ ቦታ ሰብስበው አስቀመጧቸው። የጅላ አባላቱ ለውይይት ወይም ለስብሰባ የተጠሩ ነበር የመሰላቸው። በመቀጠል የጅላ አባላቱ የያዙትን መሳሪያ አንዲያስረክቡ ተደረገ። ቤት የቀረውንም ቤቶቻቸውን እየፈተሹ ወሰዱ። የያዙት መሳሪያ ፍቃድ ያለው ነበር” ማለታቸው በሪፖርቱ ላይ ተቀምጧል።
“ ‘በሀሮ ቀርሳ የተገደሉት ፖሊሶችን ማን ነው የገደላቸው?’ እያሉ ደጋግመው እየጠየቁ በተቀመጡበት ቦታ ይዝቱባቸው ነበር። እነሱም ድርጊቱ ሌላ ቀበሌ ላይ የተፈጸመ በመሆኑ እንደማያውቁ አስረዷቸው። ፖሊሶቹ ግን ‘ካልነገራችሁን እንገድላችኋለን’ እያሉ ያስፈራሯቸው ነበር” ሲሉ እኚሁ የአይን እማኝ ለምርመራ ቡድኑ ተናግረዋል።
በዚህ አይነት መልኩ በጸጥታ አባላት ቁጥጥር ስር ከዋሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት መካከል 16 ሰዎች ወደ ጨቢ አኖሌ ጫካ ተወስደው፤ አስራ አራቱ በጥይት ተመተው መገደላቸውን ኢሰመኮ ዛሬ ባወጣው የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። መሬት ላይ እንዲተኙ ተደርገው በጥይት ተመተው ተገድለዋል ከተባሉ የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ውስጥ የከረዩ አባገዳ ከዲር ሀዋስ እንደሚገኙበት ሪፖርቱ ጠቁሟል። ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ ጫካ በመሮጥ ማምለጣቸውን ምስክሮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።
የሟቾችን አስከሬን ያነሱ እና የቀበሩ ሰዎች ለኮሚሽኑ እንደተናገሩት፤ ግድያው ወደ ተፈጸመበት ቦታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሄዱበት ወቅት በቦታው በነበሩ ፖሊሶች አስክሬኖቹን እንዳያነሱ ተከልክለው ነበር። በዚህም ምክንያት አስከሬኖቹ ለበርካታ ሰዓታት ሳይነሱ በመቆየታቸው፤ “የፈነዱ እና በከፊል በዱር እንስሳ የተበሉ ጭምር እንደነበሩ” ገልጸዋል። ሟቾቹ “ከጀርባ በኩል ወገባቸው እና ጭንቅላታቸው ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች” በአስክሬኖቹ ላይ መመልከታቸውንም ምስክሮቹ ለምርመራ ቡድኑ አስታውቀዋል።
ግድያው በተፈጸመበት ዕለት በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው ከተወሰዱ 39 የጅላ አባላት መካከል፤ ሃያ ሶስቱ ወዴት እንደተወሰዱ እንኳ ሳይታወቅ መቆየታቸው በኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት ላይ ተመልክቷል። ደብዛቸው ጠፍቶ ከነበሩ የጅላ አባላት ውስጥ ጅሎ ቦረዩ የተባለ ግለሰብ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ህይወቱ አልፎ መገኘቱም በሪፖርቱ ተገልጿል።
የሟቹ ቤተሰቦች የግለሰቡን አስክሬን በሞጆ ከተማ ከሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ወስደዋል ተብሏል። አስክሬኑን የተቀበሉ የቤተሰብ አባላት፤ በአስክሬኑ ጭንቅላት ላይ የመፈንከት፣ በተለያዩ የሰውነቱ ክፍሎች ላይ ቁስል እና የድብደባ ምልክቶች መመልከታቸውን ለኮሚሽኑ ገልጸዋል። በእስር ላይ የነበሩ ቀሪዎቹ የጅላ አባላት፤ ከሳምንታት በኋላ ከእስር መለቀቃቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል።
መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤ ግድያዎቹን በተመለከተ ከአካባቢው መስተዳድር፣ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር እና የጸጥታ ጽህፈት ቤቶች መረጃ ማሰባሰቡን እና ምላሽ መቀበሉን በሪፖርቱ ጠቅሷል። “ከከረዩ አባገዳዎች ጋር በሰላም ዙሪያ አብረው ሲሰሩ” እንደነበር የገለጸው የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር፤ “የተፈጸመው ግድያ መንግስትና ሕዝብን ለማራራቅ የተፈጸመ የጠላት/ ‘ኦነግ ሸኔ’ ሴራ” መሆኑን መናገራቸው በሪፖርቱ ሰፍሯል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በምርመራው በሰበሰባቸውና ባገናዘባቸው ማስረጃዎች 14 የከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ጭካኔ በተሞላው ሁኔታ የተገደሉበት አካሄድ፤ “ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ (extra judicial killing) ስለመሆኑ በምክንያታዊ ሁኔታ አሳማኝ (reasonable ground to believe) ሆኖ” ማግኘቱን በሪፖርቱ አጽንኦት ሰጥቷል። በሞጆ ከተማ በሚገኝ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ በቁጥጥር ስር እያለ ህይወቱ ያለፈው የጅላ አባል ጉዳይንም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸመ መሆኑን እንደሚያምን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ማጠቃለያ ባቀረበው ምክረ ሃሳብ በከረዩ የሚችሌ ገዳ አባላት ላይ ይህን የግድያ ወንጀል የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሰዎችን እንዲሁም በፖሊስ አባላት ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል የፈጸሙትን ሰዎች በሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢው የወንጀል ምርመራ በአፋጣኝ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስቧል። ለሟቾች ቤተሰቦች እና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢ የሆነ ካሳ ሊሰጣቸው እንደሚገባም አስገንዝቧል።
“ስለ ጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሰረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማህበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል”
ዶ/ር ዳንኤል በቀለ – የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር
ይህን ምክረ ሃሳብ በማስታወስ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “ስለ ጠቅላላ የነገሩ ሁኔታ እውነቱን በመግለጽ፣ ፍትሕ በማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን በመካስ ላይ የተመሰረተ አስፈላጊ ተግባራትን በማከናወን የማህበረሰቡን ሰላም እና ደህንነት እንዲመለስ ማድረግ ይጠበቃል” ብለዋል። ኢሰመኮ በምርመራው ደረስኩባቸው ባላቸው ግኝቶች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ፤ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና ለክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በደብዳቤ ቢያሳውቅም ሁለቱም መስሪያ ቤቶች ሪፖርቱ ይፋ እስከተደረገበት እለት ድረስ ምላሽ አልሰጡኝም ብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)