የኬንያው ፕሬዝዳንት የኢትዮጵያ ተፈላሚ ወገኖች ግጭት እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ

በኢትዮጵያ ውጊያ የገጠሙ ኃይሎች ሁሉ ግጭት እንዲያቆሙ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጥሪውን ያቀረቡት የኢትዮጵያ ግጭት አስመልክተው ዛሬ ረቡዕ ምሽት ባወጡት አጭር መግለጫ ነው።

በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት በኩል የወጣው ይህ መግለጫ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ትላንት ምሽት የተላለፈውን ጥሪ ያስተጋባ ነው። ጉተሬዝ በትላንቱ መግለጫቸው በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ወገኖች የኦሎምፒክ መንፈስን ታሳቢ በማድረግ “ግጭት በፍጥነት እንዲያቆሙ” ብርቱ ተማጽኗቸውን አቅርበው ነበር።

የተመድ ዋና ጸሀፊ የጠቀሱት ስፖርታዊ ውድድር፤ ከነገ በስቲያ አርብ በቻይና ቤይጂንግ የሚጀመረውን የክረምት ኦሎምፒክን ነው። የኬንያው ፕሬዝዳንት በዛሬው መግለጫቸው በተመሳሳይ ሁኔታ የኦሎምፒክን መንፈስ አንስተዋል። “የኢትዮጵያ ህዝብ በኦሎምፒክ መንፈስ ሰላምን እንዲቀበል እና ለእውነተኛ እርቅ መንገድ እንዲጠርግ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።  

ኡሁሩ በኢትዮጵያ በአፋጣኝ ግጭት እንዲቆም ጥሪ ያቀረቡት “እንደ ኬንያ ፕሬዝዳንት እና እንደ ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ወዳጅ” እንደሆነ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። ፕሬዝዳንቱ ሀገራቸውን በምትጎራበተው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ነው ያሉት ግጭት፤ “በታላቂቱ አገር ባህል እና ስልጣኔ አብሮ የተሸመነውን ክብር” ከሀገሪቱ “ህዝብ ላይ መንሳቱን ቀጥሏል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ፣ ጸጥታ እና መረጋጋት ሊረጋገጥ የሚችለው በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ኃይሎች “ፈተናዎችን ዘላቂ እና በሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ባለው መንገድ ሲወጡ ብቻ” እንደሆነ የኬንያው ፕሬዝዳንት ገልጸዋል። በማመቻመች እና ሀሳቦችን በማስተናገድ የሚካሄድ ሁሉን አካታች ብሔራዊ ውይይት በዚህ ረገድ መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ጠቁመዋል። ብሔራዊ ውይይቱ “በመላው ኢትዮጵያ ተጽዕኖ ለደረሰባቸው ሰዎች የግጭትን ጫና ሊያቃልል እንደሚችል” ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)