የአማራ ክልል፤ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የሚያደራጅ እና የሚገነባ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አቋቋመ

በሃሚድ አወል

የአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የሚያደራጅ እና የሚገነባ ጽህፈት ቤት አቋቋመ። ጽህፈት ቤቱ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ዕቅድ ከማውጣት ጀምሮ ሀብት እስከማሰባሰብ እና የመልሶ ግንባታ ስትራቴጂዎች እስከመቅረጽ ያሉ ስራዎችን ያከናውናል ተብሏል። 

“በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋምና ልማት ፈንድ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት” የሚል ስያሜ ያለውን ይህን ተቋም የሚያቋቋም ደንብ፤ የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት እሁድ ጥር 22፤ 2014 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው አጽድቋል። የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ ተጠሪነት፤ የክልሉን ርዕስ መስተዳድር፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የአስፈጻሚ ቢሮ ኃላፊዎችን በአባልነት ለያዘው ለክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት እንደሚሆን ተገልጿል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ “ይህ ተቋም በጊዜያዊነት የሚደራጀው የክልሉ አንድ ተቋም ሆኖ ነው። ራሱን ተቋሙን የሚመራ እና የሚያስተባበር የሰው ኃይል ይመደብለታል” ሲሉ ጽህፈት ቤቱ በክልሉ ምክር ቤት እንደተዋቀሩት ሌሎች አስፈጻሚ አካላት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ የሚያቋቋም እና የሚገነባው ጽህፈት ቤት የሚደራጀው “የክልሉ አንድ ተቋም ሆኖ ነው” ብለዋል [ፎቶ፦ ዋልታ ቲቪ]

የጽህፈት ቤቱ የስራ ዘመን “በጊዜያዊነት አምስት አመትን ታሳቢ ያደረገ ነው። ከአምስት ዓመት በኋላ ተገምግሞ ይቀጥል ከተባለ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በቂ ነው ተልዕኮውን ጨርሷል ከተባለ ደግሞ ሊፈርስ ይችላል” ሲሉ አቶ ግዛቸው ገልጸዋል። የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ስራው “በተደራቢነት በተልዕኮ ከሚሰራ” ይልቅ፤ ስራውን ለማቀላጠፍ በበላይነት የሚመራው አንድ ተቋም ኃላፊነቱን እንዲረከብ በማሰብ የፕሮጀክት ጽህፈት ቤቱ እንዲቋቋም መደረጉንም አስረድተዋል። 

ይህን ኃላፊነቱን ለመወጣትም ጽህፈት ቤቱ ሀብት ማሰባሰብን ጨምሮ ሌሎች ተግባራትን እንደሚያከናውንም ገልጸዋል። የፌደራል መንግስት ለመልሶ ግንባታው የመደበው ገንዘብ “በቂ አለመሆኑን” የጠቀሱት፤ አቶ ግዛቸው ጽህፈት ቤቱ “ሁሉንም አይነት የገንዘብ ምንጭ” በመጠቀም ሀብት እንደሚያሰባስብ አብራርተዋል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 20፤ 2014 ባካሄደው ልዩ ስብሰባ፤ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች 5 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ማጽደቁ ይታወሳል። ተጨማሪ በጀቱ ከመጽደቁ በፊት በተደረገው ውይይት ላይ “በጀቱ በቂ አይደለም” የሚል ተመሳሳይ አስተያየት ከፓርላማ አባላት ተነስቶ ነበር። 

የአማራ ክልል ፕላን እና ልማት ቢሮ፤ በአማጽያን ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የደረሱ የጉዳት መጠኖችን የሚያጠና ኮሚቴ አዋቅሮ ስራ ጀምሯል

ከአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ምርጫ ክልል ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው ፓርላማ የገቡት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ “በጦርነቱ ለወደሙ አካባቢዎች የተመደበው በጀት በቂ ነው ብዬ አላስብም” ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተው ነበር። ዶ/ር ደሳለኝ፤ በአፋር እና አማራ ክልሎች በመቶ ቢሊዮን የሚገመት ውድመት መድረሱን ገልጸው “ይኼን ያህል ውድመት ለደረሰባቸው አካባቢዎች 5 ቢሊዮን ብር ለመልሶ ግንባታ (reconstruction) በቂ ነው ወይ?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበው ነበር። 

የፓርላማ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር እዮብ ተካልኝ፤ ለመልሶ ግንባታው 5 ቢሊዮን ብር በቂ አለመሆኑን ገልጸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል አማካኝነት የሀብት ማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

የአማራ ክልል ያቋቋመው የመልሶ ግንባታ እና ማቋቋም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት፤ በክልሉ መንግስት በሚመደብለት በጀት ስራዎቹን እንደሚያከናውን አቶ ግዛቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ፤ በአማጽያን ኃይሎች ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የደረሱ የጉዳት መጠኖችን የሚያጠና ኮሚቴ አዋቅሮ ስራ ጀምሯል። ይህ ጥናት “እየተገባደደ” መሆኑን እና አዲስ ለተቋቋመው ጽህፈት ቤት ግብዓት እንደሚሆን የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)