በአፋር እና አማራ ክልሎች በጦርነት ከተጎዱ የጤና ተቋማት መካከል ከግማሽ በላዩ አገልግሎት እንዳልጀመሩ ጤና ሚኒስቴር ገለጸ

በሃሚድ አወል

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ በአፋር እና አማራ ክልሎች ጉዳት ከደረሰባቸው የጤና ተቋማት ውስጥ “መሰረታዊ የሆኑ የህክምና አገልግሎቶች” መስጠት የጀመሩት ከግማሽ በታች መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። በሁለቱ ክልሎች 2,924 የጤና ተቋማት ውድመት እና ዝርፊያ እንደደረሰባቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

የጤና ሚኒስቴር የወደሙ ተቋማትን አሃዝ ይፋ ያደረገው፤ ዛሬ አርብ ጥር 27 የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ነው። ሪፖርቱን ለፓርላማ ያቀረቡት የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንዳሉት፤ በሁለቱ ክልልች ውድመት ከደረሰባቸው 2,924 የጤና ተቋማት መካከል “መሰረታዊ የሆኑ የህክምና አገልግሎቶችን” መስጠት ጀመሩት 1,217 ብቻ ናቸው። 

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት መሰረት፤ በአፋር እና አማራ ክልሎች ውድመት ከደረሰባቸው 42 ሆስፒታሎች መካከል 37ቱ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በሁለቱ ክልሎች ከሚገኙ 523 የጤና ጣቢያዎች መካከል በ290ዎቹ አገልግሎት ማስጀመር መቻሉ በሪፖርቱ ተገልጿል። በጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው 2,359 የጤና ኬላዎች ውስጥ ወደ አገልግሎት የተመለሱት ግን 890 ብቻ መሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።  

ዶ/ር ሊያ ታደሰ ቀሪ የጤና ተቋማትን አገልግሎት የማስጀመር ስራን በተመለከተ ለፓርላማ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፤ “ሙሉ በሙሉ በአጭር ጊዜ ይሄን ማድረግ አስቸጋሪ ስለሆነ በምዕራፎች ተከፋፍሎ ስራው እየተሰራ ነው። ቁልፍ የሚባሉ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል። 

ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እና ሌሎች የጸጥታ ችግሮች የህክምና አገልግሎቶች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን በጤና ሚኒስቴር ሪፖርት ላይ ተመላክቷል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ “የጤና ግብዓቶች እና በጀቶች ለድንገተኛ ህክምና መዞራቸው የጤና ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል” ሲል ጦርነቱ ያስከተለውን ተጽዕኖ በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።

በሪፖርቱ መሰረት የጦርነቱ ተጽዕኖ ጎልቶ የታየው በጸረ-ኤች አይ ቪ የህክምና አገልግሎት ላይ ነው። የጤና ሚኒስቴር የአዋቂዎችን የጸረ-ኤች አይ ቪ የህክምና አገልግሎት ከ92 በመቶ ወደ 95 በመቶ የማሳደግ ግብ የነበረው ቢሆንም አገልግሎቱን ያገኙት ግን 82 በመቶ ብቻ ናቸው። ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር ማሽቆልቆል በሪፖርቱ በምክንያትነት የተጠቀሱት “በጦርነቱ በተጎዱ አካባቢዎች የደረሰው መፈናቀል፤ የጤና ተቋማት ውድመት እና የጸረ-ኤች አይ ቪ መድሃኒት ህክምና አገልግሎት መቋረጥ” ናቸው።

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፤ የጤና ሚኒስቴር ከልማት ድርጅቶች የሚሰበስበው ድጋፍ ላይም ቀጥተኛ ተጽዕኖ አሳርፏል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው 117 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ውስጥ ባለፉት ስድስት ወራት መሰብሰብ የቻለው ከግማሽ ያነሰውን 55.9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ለፓርላማ አባላት እንደተናገሩት፤ ለሀብት አሰባሰቡ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ለጋሽ ሀገራት ሁለት ምክንያቶችን አቅርበዋል። የመጀመሪያው ምክንያት፤ ድጋፍ ለማድረግ እሺታቸውን ገልጸው የነበሩ ሀገራት ቃል የገቡትን በጀት “ለሰብዓዊ ድጋፍ አዙረነዋል” ማለታቸው ነው። ሁለተኛው ምክንያታቸው ደግሞ በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የተነሳ በበጀቱ ቃል የተገባላቸው ስራዎች “ በእቅዳቸው መሰረት ሊሰሩ አይችሉም” የሚል ነው።

የጤና ሚኒስቴር፤ ከገንዘብ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች ጋር በመሆን ጉዳዩን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)