የ42 ዕጩ ኮሚሽነሮች ማንነት ታወቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ ለኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በዕጩነት ከተጠቆሙ ግለሰቦች መካከል፤ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ “በተቀመጠው መስፈርት የተለዩ ናቸው” ያላቸውን 42 ዕጩ ኮሚሽነሮችን ማንነት ዛሬ አርብ ጥር 27 ይፋ አደረገ። ዕጩዎቹ የተለዩት ለኮሚሽነርነት ከተጠቆሙ 632 ግለሰቦች መካከል ነው።  

ከዕጩ ኮሚሽነሮቹ መካከል አስራ ሶስቱ ፕሮፌሰሮች ሲሆኑ አስራ ሁለቱ ደግሞ የዶክትሬት ማዕረግ ያላቸው ናቸው። ዛሬ ይፋ በተደረገው የዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ አራት የቀድሞ አምባሳደሮች ተካትተዋል። 

ከአርባ ሁለቱ ዕጩዎች ውስጥ አራት ብቻ ሴቶች መሆናቸው ዛሬ ከሰዓት በተወካዮች ምክር ቤት በነበረ የህዝብ አስተያየት መስብሰቢያ መድረክ ላይ አነጋግሯል። አምባሳደር ታደለች ኃ/ሚካኤል፣ ዶ/ር አይሮሪት መሐመድ ያሲን፣ ወ/ሮ ሂሩት ገ/ስላሌ እና ወ/ሮ ዘነበወርቅ ታደሰ ለኮሚሽነርነት በዕጩነት የቀረቡ ሴቶች ናቸው። 

በአገራዊ የምምክር ኮሚሽኑ የሴቶች ተሳትፎ አናሳ ይሆናል የሚል ስጋት የገባቸው 20 የሲቪክ ማህበራት፤ ለኮሚሽነርነት በዕጩነት ከሚቀርቡ የመጨረሻ 14 ግለሰቦች መካከል ግማሽ ያህሉ ሴቶች እንዲሆኑ ባለፈው ሳምንት ጥያቄ አቅርበው ነበር። የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩት በማቋቋሚያ አዋጁ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)