ተመድ በሶማሊያዋ ዶሎ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል እንዲያቋቁም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ጠየቁ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው የሶማሊያዋ ዶሎ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል እንዲያቋቁም የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ጠየቁ። ርዕሰ መስተዳድሩ ሀሳቡን ያቀረቡት፤ ከሶማሊያ የሚነሱ ስደተኞች በድርቅ ምክንያት ከፍ ያለ ፈተና ወደተጋረጠበት የሶማሌ ክልል ገብተው ተጨማሪ ጫና እንዳይፈጠሩ ለመከላከል ነው።

አቶ ሙስጠፌ ትላንት እሁድ ምሽት ጥር 29 በተረጋገጠ የማህበራዊ ገጾቻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የሶማሌ ክልል አስቸጋሪ የድርቅ ሁኔታን በተጋፈጠበት በዚህ ጊዜ ከሶማሊያ ተጨማሪ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ከተሻገሩ፤ “ቀድሞም በተወጠረው እርዳታ የማቅረብ አቅም እና በመሰረታዊ አገልግሎት ላይ ጫና ይፈጥራል” ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለዚህ ችግር ያቀረቡት መፍትሔ፤ ከሶማሊያ መሰደድ የሚሹ የሀገሪቱ ዜጎች በድንበር አካባቢ እንዲቆዩ ማድረግ ነው። “ተጨማሪ ሰዎች ዓለም አቀፉን ድንበር ተሻግረው ስደተኛ እንዳይሆኑ ለመከላከል UNHCR በሶማሊያ ዶሎ የመቀበያ ማዕከል ማቋቋም አለበት” ብለዋል አቶ ሙስጠፌ።

ዶሎ ከኢትዮጵያ ድንበር በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሶማሊያ ጌዶ ግዛት የምትገኝ አነስተኛ ከተማ ነች። ከድንበሩ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሶማሌ ክልል የዶሎ አዶ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል ይገኛል።

የተመድ የስደተኞች መርጃ ከፍተኛ ኮሚሽን በዶሎ ኦዶ አነስተኛ ከተማ የስደተኞች መቀበያ ማዕከል አቋቁሞ አገልግሎት መስጠት የጀመረው በ2001 ዓ.ም. ነበር። በወቅቱ ከሶማሊያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡን ተከትሎ፤ በሶስት ዓመት ውስጥ ብቻ አራት ተጨማሪ ማዕከሎች በዶሎ ኦዶ እንዲከፈቱ አድርጓል።

በUNHCR መረጃ መሰረት፤ እስካለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ ድረስ በሶማሌ ክልል የዶሎ ኦዶ የስደተኞች መቀበያ ማዕከልን ጨምሮ በሶማሌ ክልል ባሉ ስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ሶማሊያውያን ብዛት 180 ሺህ ገደማ ነበር። በሶማሊያ አራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በመስተጓጎላቸው ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ 3.2 ሚሊዮን የሀገሪቱ ዜጎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ አስታውቋል።  

በድርቅ የተጎዱ የሶማሊያ ዜጎች ከሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ወደ ከተሞች መፍለሳቸውን የጽህፈት ቤቱ መግለጫ አስታውቋል። የተወሰኑቱ ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ፍለጋ ድንበር አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ መጀመራቸውን ጽህፈት ቤቱ ከሶስት ሳምንት በፊት ባሰራጨው ሪፖርት ጠቅሷል። የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፤ በትላንቱ መልዕክታቸው በዶሎ አዶ ለሚገኙ 760 ስደተኞች የሊበን ዞን አስተዳዳሪዎች እርዳታ ማቅረባቸውን በፎቶግራፍ ማስረጃዎች አስደግፈው ገልጸዋል። 

ስደተኞቹ የእርዳታ ፍለጋ የሸሹበት የኢትዮጵያው የሶማሌ ክልልም ቢሆን በተመሳሳይ መልኩ በዝናብ ወቅቶች መስተጓጎል ምክንያት ብርቱ ድርቅ ከገጠማቸው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች አንዱ ሆኗል። የረድኤት ድርጅቶ የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በደቡባዊ ኢትዮጵያ የአርብቶ አደር አካባቢዎች፣ ሰሜን ምዕራብ ኬንያ እንዲሁም የደቡብ እና ማዕከላዊ ሶማሊያ ሰፊ አካባቢዎችን ያካለለው ድርቅ ባለፉት 40 ዓመታት ከታዩት “አስከፊው ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

በኢትዮጵያ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች ወደ 6.8 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተመድ የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባለፈው ሳምንት አስታውቆ ነበር። በእንሳስት መኖ እና ውሃ እጥረት ሳቢያ በእነዚህ አካባቢዎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የቀንድ ከብቶች መሞታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)