ንግድ ባንክ አምስት ሺህ ገደማ ሰራተኞቹን አዲስ ወደሚያስመርቀው የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ሊያዛውር ነው

በሀሴት ሀይሉ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የሚሰሩ አምስት ሺህ ገደማ ሰራተኞቹን፤ በመጪው እሁድ ወደሚያስመርቀው ባለ 48 ፎቅ የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ ሊያዛውር ነው። ስምንት ቢሊዮን ብር ገደማ የወጣበት እና ሰባት ዓመት የፈጀው የግዙፉ ህንጻ ምርቃት፤ ከባንኩ የ80ኛ አመት የምስረታ በዓል ጋራ በጣምራ እንደሚከበር ባንኩ አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ በምረቃ ስነ-ሥርአቱ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም ለተቋሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎች ይታደማሉ። በዚሁ ስነ ስርዓት ላይ፤ ለባንኩ ስኬታማነት አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሰራተኞች እና በዋና መስሪያ ቤቱ ህንጻ ግንባታ ላይ ለተሳተፉ ሰራተኞች እውቅና ይሰጣል ብለዋል።

በዕለቱ ከህንጻው ምረቃ ጎን ለጎን የሚካሄደው የባንኩ የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነም አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባንኩ በስምንት አስርት ዓመታት ጉዞው ያጋጠመውን ውጣ ውረድ እንዲሁም ስኬቶችን የሚያሳይ አውደ ርእይ በዕለቱ በይፋ እንደሚከፈትም ጠቁመዋል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ባንክ በሚል ስያሜ የተመሰረተው በነሐሴ 1934 ዓ.ም. ነው። ባንኩ አሁን ያለውን ስያሜ ያገኘው ከተመሰረተ ከ24 ዓመታት በኋላ በ1958 ዓ.ም ነበር። በዚያን ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ብሔራዊ ቴአትር አካባቢ የሚገኘውን እና በተለምዶ “ወርቃማው ባንክ” እየተባለ የሚጠራውን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። 

ንግድ ባንክ አሁን በዋና መስሪያ ቤትነት የሚጠቀምበትን እና የባንኩን ፊንፊኔ ቅርንጫፍ የያዘው ህንጻ ለአገልግሎት ክፍት ያደረገው በ1977 ዓ.ም ነበር። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዚህ ሳምንት የሚያስመርቀውን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ለማስገንባት የቻይና መንግስት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (CSCEC) ጋር ስምምነት የተፈራረመው በ2007 ዓ.ም እንደነበር ይታወሳል። 

በቀጣዩ ዓመት ግንባታው የተጀመረው ይህ ግዙፍ ህንጻ እስከ 2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፤ ለምርቃት የደረሰው ተጨማሪ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ወስዶ ነው። የባንኩ ህንጻ ግንባታ ሲጀመር 46 ወለል እንደሚኖረው ታስቦ እንደነበረ የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤ በስተኋላ በተደረገ የዲዛይን ለውጥ ወለሉ ወደ 48 ከፍ እንዲል መደረጉ እና አዳዲስ ሥራዎች መታከላቸው ግንባታው ከታቀደለት ጊዜ በላይ እንዲወስድ እንዳደረገው ያስረዳሉ።

በህንጻ ግንባታው የማጠናቀቂያ ጊዜ ላይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱም ለግንባታው መዘግየት ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት ይገልጻሉ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለው ተጽዕኖ፣ የግንባታ ዋጋዎች ዕቃዎች ጭማሪ እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ማሻቀብ፤ ለህንጻው ግንባታ የወጣውን ወጪ አንሮታል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግዙፉን የዋና መስሪያ ቤቱን ህንጻ ለማስገንባት በመጀመሪያ የመደበው በጀት 5.6 ቢሊዮን ብር እንደነበር ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ አቶ ኤፍሬም ገለፅ ህንጻውን ሙሉ ለሙሉ ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከ7 እስከ 8 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ወጪ ፈጅቷል። 

ተጨማሪ ወጪው በባንኩ ላይ ስላሳደረው ተጽዕኖ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት፤ “ግንባታው ተጠናቆ ለመመረቅ የተዘጋጀው ህንጻ ላይ ወደ 2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ተጨማሪ ገንዘብ መጨመር በባንኩ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አይፈጥርም። ምክንያቱ ደግሞ በአነስተኛ ወጪ ትልቅ ፕሮጀክት ነው የተሰራው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

በአዲስ አበባ ፍልውሃ አካባቢ ከኢትዮጵያ ሆቴል ጎን ባለው ስፍራ የተገነባው አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንጻ፤ በተለያዩ ቦታዎች ተበታታትነው ይሰሩ የነበሩ ከአምስት ሺህ በላይ የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞችን በአንድ ላይ የሚያሰባስብ ነው ተብሏል። የባንኩ ፕሬዝዳንት፣ የምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ ስራ አስኪያጆች እና ሌሎችም ሰራተኞች ከሁለተኛ እስከ 46ኛ ባሉት ወለሎች ላይ እንደሚደለደሉም ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

“የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ቁጥራቸው በጣም በርካታ ነው። ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የዋና መስሪያ ቤት ክፍል ሰራተኞች አሉን። አሁን ባለው ሁኔታ ባንኩ በርካታ ህንፃዎችን ተከራይቶ ነው የሚጠቀመው። እናም ከኪራይ የምንወጣበትን በዋናነት ቅድሚያ ሰጥተን ነው የምንሰራው። በዚህም በተለያዩ ቦታዎች ተበታትኖ የሚገኙ የዋና መስሪያ ቤት ሰራተኞች ወደ አዲሱ ህንፃ ይገባሉ። ይህም ባንኩ በየወሩ ለኪራይ የሚያወጣውን ወጪ ይቀንሰዋል” ሲሉ ምክትል ፕሬዝዳንቱ የባንኩ ሰራተኞች ወደ አዲሱ ህንጻ መዛወር ያለውን ጥቅም አብራርተዋል።

ባንኩ የአዲሱን ህንጻ የመጀመሪያው ወለል ያዋለው፤ የባንኩን ታሪክ የሚያመላክት የማሳያ ሥፍራ አድርጎ ነው። የህንጻው 47ኛ ወለል ለሬስቶራንት አገልግሎት የሚውል ሲሆን፤ 48ኛው ደግሞ ከአራቱም አቅጣጫ ከተማዋን ለማሳየት በሚያስችል መልኩ እንደገና ዲዛይን ተደርጎ ተገንብቷል። የዋና መስሪያ ቤቱ ህንጻ፤ ለ1,500 መኪኖች ማቆሚያነት የሚያገለግሉ ከምድር በታች የተገነቡ አራት ወለሎች አሉት። 

 በ165,476 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲሱ ዋና መስሪያ ቤት፤ ከዋናው ህንጻ በተጨማሪ ስድስት እና ስምንት ፎቆች ያሏቸው ሁለት ተደራቢ ሕንፃዎችን ይዟል። በአንደኛው ተደራቢ ህንጻ ሁለት ሺህ ሰዎች ማስተናገድ የሚችል ሰፊ የስብሰባ አዳራሽ ተገንብቷል። 

ተደራቢ ህንጻው እያንዳንዳቸው 300 ሰዎች የሚይዙ ሁለት አዳራሾች እና እያንዳንዳቸው 200 ሰዎች የሚያስተናግዱ አምስት የስብሰባ አዳራሾችንም በተጨማሪነት አካትቷል። በዚሁ ህንጻ ላይ መደበኛ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥበት ቅርንጫፍ ይኖራልም ተብሏል።   

ሁለተኛው ተደራቢ የህንጻ ክፍል ደግሞ፤ ለተለያዩ የንግድ ስራዎች ማለትም ለሬስቶራንቶች፣ ለንግድ ሱቆች፣ ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ፣ ለህፃናት ማቆያ የሚሆኑ ቦታዎችን የያዘ ነው። ይህ ተደራቢ ህንጻ ስድስት ያህል ሲኒማ ቤቶችን በውስጡ እንደሚኖሩትም መሆኑን የባንኩ ምክትል ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  በዚህ ህንጻ የሚገኙ አገልግሎት መስጪያ ቦታዎችን ባንኩ ለኪራይ እንደሚያውላቸውም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)