የቀድሞ ፓርላማ አባላት በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ የተላለፈው ውሳኔ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ታገደ

በሃሚድ አወል

ባለፈው ሰኔ ወር የምርጫ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ በመንግስት ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ ተላልፎ የነበረው ውሳኔ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ታገደ። እግዱን ዛሬ ያስተላለፈው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ ጉዳዩ በችሎት የሚያስቀርብ በመሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ምላሽ እንዲሰጡ አዝዟል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከነበሩት 547 ተመራጮች መካከል፤ በመንግስት የተሰጣቸውን ቤት እንዲለቅቁ በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የተላለፈውን ትዕዛዝ በመቃወም ለፍርድ ቤት አቤት ያሉት 163 የሚሆኑት የቀድሞ የፓርላማ አባላት ናቸው። የቀድሞ የፓርላማ አባላቱ በቅድሚያ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነበር። 

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ ከመንግስት ቤት የማስለቀቅ ትዕዛዙን ያስተላለፈው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በፍርድ ቤት ቀርቦ ምላሽ መስጠት አይገባውም” የሚል ውሳኔ በማስተላለፉ ጉዳዩ ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተወስዷል። ጉዳዩን የተመለከተው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሰኞ 23 በዋለው ችሎት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አጽንቷል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዕለቱ ባስተላለፈው ውሳኔም፤ ተሰናባች የምክር ቤት አባላቱ “በመንግስት በተሰጣቸው ቤት ውስጥ ቆይተው የሚከራከሩበት የህግ መሰረት የለም” በሚል ከተሰጣቸው ቤት እንዲወጡ ወስኖ ነበር። በዚህ ውሳኔ ቅር የተሰኙት 163ቱ የቀድሞ ፓርላማ አባላት በማግስቱ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባስገቡት ደብዳቤ፤ ውሳኔው እንዲታገድላቸው አቤቱታ አቅርበዋል። 

የፓርላማ አባላቱ በዚሁ አቤቱታቸው፤ “ከቤታችን ውጡ ተብለን ማስጠንቀቂያ ደርሶናል። ስለዚህ ከቤት ስንወጣ ሊተካ የማይችል ጉዳት ሊደርስብን የሚችል በመሆኑ በዚህ ፍርድ ቤት ያቀረብነው በሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ውጤቱ እስከሚታወቅ ድረስ ለጊዜው እግድ ይሰጥልን” ሲሉ ጠይቀዋል።

አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የተሰናባች ፓርላማ አባላቱ የሰበር አቤቱታ ተመርምሮ ውጤቱ እስከሚታወቅበት ድረስ፤ መንግስት ከሰጣቸው ቤት እንዲወጡ እስከ ጥር 30 ድረስ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ታግዶ እንዲቆይ አዝዟል። ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለመመልከትም፤ ቀነ ገደቡ በሚጠናቀቅበት ዕለት ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

በቀጠሮው መሰረት ትላንት ሰኞ ጥር 30፤ 2014 የተሰየመው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ 3ኛ አጣሪ ችሎት፤ የ163ቱ የቀድሞ የፓርላማ አባላት ጠበቃ የሆኑት አቶ አንዷለም በእውቀቱ ያቀረቡትን ማብራሪያ አድምጧል። የአቤቱታ አቅራቢዎቹ ጠበቃ፤ ሁለት የምርጫ ዘመን ወይም ከዚያ በላይ ያገለገሉ የፓርላማ አባላት ከመንግስት ቤት በኪራይ የማግኘት መብት እንዳላቸው በአዋጅ መደንገጉን አንስተዋል።

“መንግስት የሚባለው ወይ ህግ አውጪው ነው፣ ወይ ህግ ተርጓሚው ነው፣ ወይም ህግ አስፈጻሚው ነው” ያሉት ጠበቃው፤ ተሰናባች የፓርላማ አባላቱን ከሚኖሩበት ቤት እንዲወጡ ያዘዘው “ህግ አውጪው አካል” መሆኑን ጠቅሰዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በስር ፍርድ ቤት በነበረ ክርክር፤ “ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት የህግ አስፈጻሚው ነው” ማለቱ “ተገቢ አይደለም” ብለዋል። 

ሁለት ዙር እና ከዚያ በላይ ያገለገሉት የቀድሞ የፓርላማ ተመራጮች “የማይቆራረጥ መብት አላቸው” ያሉት አቶ አንዷለም፤ ተመራጮቹ ላቀረቡት ጥያቄ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሰጠው ምላሽ ይህንን መብት የሚጋፋ ነው ብለዋል። የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት በዚሁ ምላሹ፤ ተመራጮቹ ጥያቄያቸውን “አሁን ከሚኖሩበት ቤት ወጥተው ይጠይቁ” ማለቱን ያስታወሱት ጠበቃ፤ ይህ “ለአባላቱ በአዋጅ የተደነገጉትን መብቶች የሚጥስ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል። 

የጠበቃውን ማብራሪያ ያደመጠው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ ማክሰኞ የካቲት 1 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። ፍርድ ቤቱ ዛሬ በጽህፈት ቤት በኩል በሰጠው ብይን፤ ከሰባት ቀናት በፊት የተላለፈው እግድ ጸንቶ እንዲቆይ ወስኗል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤትም፤ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ምላሽ በሬጅስትራር በኩል እስከ የካቲት 25፤2014 በጹሁፍ እንዲያስገቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል። 

ይህንን የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ዛሬ ረፋድ በስፍራው ተገኝተው የሰሙት የምክር ቤት አባላት ደስታቸውን ሲገልጹ ተስተውለዋል። የተወሰኑ አባላት ደስታቸውን በለቅሶ ሲገልጹ በቦታው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። የቀድሞ የፓርላማ አባላቱን እንዲህ ስሜታዊ ያደረጋቸው፤ በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አማካኝነት በመኖሪያ ቤታቸው ተለጥፎ የነበረ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለፈጠረባቸው ጭንቀት ጊዜያዊ መፍትሔ በማግኘታቸው ነው። 

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ማህተም ያረፈበት ይህ ደብዳቤ፤ የቀድሞ የፓርላማ አባላት የሚኖሩባቸውን ቤቶች እስከ ጥር 30 እንዲያስረክቡ የሚያዝ ነበር። የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተባለው ቀን ቤቱን ክፍት አድርገው የማይጠብቁ ከሆነ፤ “የቤት ቁልፍ ተሰብሮ የንብረት ርክክብ እንደሚከናወን” ደብዳቤው አስጠንቅቋል። 

የማስጠንቀቂያ ደብዳቤው “ያሳሰባቸው” የቀድሞ የፓርላማ አባላት፤ ያለፉትን ቀናት ያሳለፉት የኪራይ ቤት ሲያፈላልጉ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ተሰናባች የፓርላማ አባል፤ ከዛሬው የፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ለእርሳቸው እና ለቤተሰባቸው መኖሪያ የሚሆን የኮንዶሚኒየም ቤት ለመከራየት “ጫፍ ላይ” ደርሰው እንደነበር ገልጸዋል።  

ስምንት የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ሌላ ተሰናባች የምክር ቤት አባልም፤ ዛሬ ከሰዓት ቀብድ ለመክፈል ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ተናግረዋል። ከኦሮሚያ ክልል ተወክለው የነበሩ የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አባል፤ “ጎዳና ላይ እንዳንወድቅ በሚል 3 ሺህ ብር ቀብድ ከፍያለሁ” ሲሉ ቤት ለመከራየት የሄዱበትን ርቀት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)