አብን፤ በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ነው ላለው “የሽብር እና የዘር ማጥፋት ወንጀል” መንግስትን ተጠያቂ አደረገ

በሃሚድ አወል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “በመንግስት የአመራር ደንታ ቢስነት እና ተሳትፎ”፤ በኦሮሚያ ክልል “የሽብር እና የዘር ማጥፋት ወንጀል” እየተፈጸመ ነው ሲል ወነጀለ። ተቃዋሚው የፖለቲካ ድርጅት ጥቃት ለደረሰባቸው ተበዳዮች ካሳ እንዲከፈል እንዲሁም ጥቃቱን የፈጸሙ አካላትም ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

አብን ትችቱን እና ጥያቄውን ያቀረበው፤ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 2፤ 2014 ረፋድ ላይ ባወጣው መግለጫ ነው። ንቅናቄው በመግለጫው ትኩረት ከሰጣቸው ሁለት ጉዳዮች መካከል አንደኛው በኦሮሚያ ክልል በአማራ ተወላጆች ላይ በተደጋጋሚ ይፈጸማሉ ያላቸውን “ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል እና ንብረት ማውደምን” የሚመለከት ነው።

እነዚህ ድርጊቶች በኦሮሚያ ክልል “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ” መምጣታቸውን የገለጸው አብን፤ ጥቃቶቹ “የሽብር፣ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት” ወንጀሎች መሆናቸውን በመግለጫው አስታውቋል። “ህዝባችን በአንድ በኩል በከፋው የጥፋት ኃይል ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል በሚልና የወንጀልና የሴራ ጥምረቶችን ታሳቢ በማድረግ፤ ሌላው ችግር በሂደት ሊሻሻል ይችላል በሚል ግምት እና ለሀገር አንድነት ቅድሚያ በመስጠት ብሶቱን አምቆና ዝምታን መርጦ ከርሟል” ያለው አብን ሆኖም “ዘር ተኮር ጭፍጨፋው ፍጹም ሊያባራ አልቻለም” ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

ለዚህም ከሰሞኑ በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች 81 የአማራ ተወላጆች መገደላቸውን በማሳያነት ጠቅሷል። ከእነዚህ የጥቃቱ ሰለባዎች በተጨማሪ “በጅምላ ተገድለው አስከሬናቸው አንድ ቦታ የተገኙ” 87 ሰዎች መኖራቸውን የገለጸው አብን፤ በአካባቢው “በድምሩ 168 ወገኖች መገደላቸው ተረጋግጣል” ሲል አክሏል።    

አብን ለሰሞኑ ጥቃትም ሆነ በኦሮሚያ ክልል ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ተጠያቂ ያደረገው፤ “አሸባሪ” ሲል የጠራውን የ“ሸኔ” ቡድንን ነው። “ወንጀሉ የሚፈጸመው በከፊሉ የመንግስት አመራር ደንታ ቢስነት እና በከፊሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ የመሆኑ ጉዳይ ችግሩን ውስበስብ ያደርገዋል” ያለው አብን፤ የመንግስት መዋቅር የሚጠበቅበትን ስራ አለመስራቱ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ጠቁሟል።  

“በአሁኑ ወቅት ህዝባችን የሚያስፈልገው በህይወት የመኖር መብቱን የሚያስከብርለት ዝቅተኛ መንግስት (minimial state) እንጂ ነባራዊ ተጨባጭነት የሌለው መዋቅር እንዳልሆነ መገንዘብ ይገባል” ሲል በመግለጫው አጽንኦት የሰጠው አብን፤ “እንደተለመደው ህዝቡ ጥቃቶችን እየተቀበለ ብቻ ይቀጥላል የሚል ግምት ስህተት እና ተገቢነት የሌለው መሆኑን መረዳት ይገባል” ሲል ማሳሰቢያ አዘል መልዕክቱን ለሚመለከታቸው አካላት አስተላልፏል።

ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የጊዳሚ ወረዳውን ጥቃት በተመለከተ ትላንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ጥቃቱ የተፈጸመው በመንግስት መዋቅር ድክመት መሆኑን አመልክቷል። ጥቃቱ “በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተባባሪነት እና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፍላጎት ያለመኖሩ ማሳያ ነው” ብሏል።

ኢዜማ በዚሁ መግለጫው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን “መግለጫ ከመስጠት እና መጽናናትን ከመመኘት የዘለለ ተጨባጭ ስራ መስራት ያልቻለ” ሲል ገልጾታል። በርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሚያ ክልል መንግስት “በክልሉ እየተፈጸሙ ላሉት አሰቃቂ ግድያዎች ተጠያቂነት አለበት” ሲልም ወንጅሏል።

አብን በዛሬው መግለጫው ያነሳው ሌላኛው ጉዳይ፤ የህወሓት ኃይሎች በአፋር ክልል እያካሄዱት ነው የተባለው የ“ዳግም ወረራ” ጉዳይን ነው። የአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ከአምስት ቀናት በፊት፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥር 28፤ 2014 ባወጣው መግለጫ፤ የህወሓት ኃይሎች በአምስት ወረዳዎች እና በአንድ የከተማ መስተዳድር ላይ ጦርነት መክፈታቸውን አስታውቆ ነበር።

የህወሓት ኃይሎች ጦርነቱን የከፈቱት “ሰርዶን በመያዝ የኢትዮ ጂቡቲን መስመር ለመቆጣጠር እና አፋርን እንደ መደራደሪያ ለመጠቀም” መሆኑን የአፋር ክልል መንግስት በወቅቱ ገልጿል። ይህን የክልሉን መንግስት መግለጫ ዋቢ ያደረገው አብን፤ “የፌደራሉ መንግስት ለአፋር ህዝብ አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጥ እና እገዛ እንዲያደርግ” ጥያቄ አቅርቧል። 

የህወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል በቆቦ እና ጠለምት አካባቢዎችም “ተመሳሳይ ወረራ እና መስፋፋት ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጅት” እያደረጉ መሆኑን የጠቀሰው አብን፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በቆቦ የተጠለሉ ከ50 ሺህ በላይ ሰዎችም ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል ብሏል። “በራያና ጠለምት ህዝብ ላይ እየሆነ ያለው ድርብርብ ቀውስ አፋጣኝ መንግስታዊ ትኩረት የሚሻ ነው” ያለው አብን፤ መንግስት በአካባቢው ትኩረት እንዲያደረግ “አጥብቀን እንጠይቃለን” ሲል የጉዳዩን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)