በአባይ ድልድልይ አቅራቢያ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ተዘግቶ የነበረው አውራ ጎዳና ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

በሃሚድ አወል

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት አንድ አሽከርካሪ መገደሉን ተከትሎ ተዘግቶ የነበረው አውራ ጎዳና፤ ዛሬ ረፋድ ጀምሮ ክፍት ሆኖ አገልግሎት መስጠት መቀጠሉን የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ተናገሩ። ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል የሚወስደው አውራ ጎዳና እንዲዘጋ ምክንያት የሆነውን ጥቃት የሰነዘሩት የ“ሸኔ ታጣቂዎች” መሆናቸውን የፖሊስ አዛዡ ገልጸዋል።

የወረጃርሶ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ታምሩ ባይሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ አባይ ድልድይ ከመደረሱ በፊት ባለው “ኮቲቻ” በሚባል አካባቢ ጥቃት የተሰነዘረው ትላንት ማክሰኞ የካቲት 1 ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ነው። በጥቃቱ ኮንቲኔየር የጫነ ሎቤድ የጭነት መኪና አሽከርካሪ መገደሉን አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም አቅጣጫ በማሽከርከር ላይ በነበረው በዚሁ ግለሰብ ላይ የእሩምታ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ የወረዳው ፖሊሶች ምላሽ መስጠታቸውን ኢንስፔክተር ታምሩ ገልጸዋል። “እነሱ ተኩስ እንደጀመሩ የእኛም ልጆች ተኩስ ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ወደ ጫካቸው ተመለሱ” ሲሉ አብራርተዋል።  

ጥቃቱን ካደረሱት ታጣቂዎች መካከል በተኩስ ልውውጡ የተገደለ ታጣቂ ስለመኖሩ ጥያቄ የቀረበላቸው የወረዳው የፖሊስ አዛዥ “ተኩስ ሲተኮስ በጨለማ መቼም ሰው አይተህ አይደለም። ብልጭታ አይተህ ነው የምትተኩሰው። የእኛ ልጆች ሲሄዱ ምንም አላገኙም። እነሱ አስክሬን ጥለው መቼም አይሄዱም [ግን] ብዙ ተመትተዋል የሚል ግምት ነው ያለን” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

በአባይ ድልድይ አቅራቢያ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች፤ ከዚህ ቀደምም በአሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲሰነዘሩ መቆየታቸው ይታወሳል። በዚህም ምክንያት አሽከርካሪዎች በአካባቢው ከምሽቱ 12 ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ተደርጎ ነበር። የወረዳው ፖሊስ አዛዥም “ይኼንን ስለምንፈራ፤ ስጋት ስላለን፤ ከ12 ሰዓት በኋላ እንቅስቃሴ በፊትም አናደርግም” ሲሉ ይህንን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል። 

በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ስጋት ለመቅረፍ “በአቅማችን የምንችለውን እያደረግን” ነው የሚሉት ኢንስፔክተር ታምሩ፤ ትላንት አመሻሽ ላይ ጥቃት በደረሰበት አካባቢም ተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች መመደባቸውን ጠቁመዋል። ለአባይ ድልድይ ጥበቃ ከሚያደርጉት የፌደራል ፖሊስ አባላት በተጨማሪ፤ የወረዳው ፖሊስ አባላት እና የአካባቢው ሚሊሺያዎች በአሁኑ ወቅት በቦታው ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የወረጃርሶ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ተጨማሪ “ኃይል አስቀምጠናል” ቢሉም፤ አሁንም አካባቢው ከስጋት ነጻ ባለመሆኑ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክረዋል። “ጠላት አድፍጦ ሰዓት ጠብቆ ሰለሚመጣ፤ የትኛው ጋር ተደብቆ ጉዳት እንደሚያደርስ ስለማይታወቅ [አሽከርካሪዎች] ማታ ባይጓዙ የተመረጠ ይሆናል” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)