የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊዘዋወር ነው

በሃሚድ አወል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ከፌደራል ፖሊስ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሊዘዋወር ነው። የከተማይቱ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ ተጠሪነቱን ለማስተላለፍ ሲከናወን የነበረው ጥናት ተጠናቅቆ ለመንግስት መቅረቡን ተናግረዋል።  

ዶ/ር ቀነዓ ይህን የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ትላንት ሐሙስ የካቲት 3፤ 2014 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን በተመለከተ ከአንድ የምክር ቤት አባል ለተነሳ አስተያየት በሰጡት ማብራሪያ ነው። ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የተባሉ እኚህ የምክር ቤት አባል፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ተጠሪነት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሆን የማድረጉ ስራ “ትኩረት ተሰጥቶት በፍጥነት መከናወን አለበት” ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።   

ለምክር ቤት አባሉ አስተያየት መነሻ የሆነው፤ የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ስለ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ያቀረቡት ገለጻ ነው። ከንቲባ አዳነች በዚሁ ሪፖርታቸው ላይ “የከተማዋን ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በተሟላ ደረጃ ለመስራት”፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አደረጃጀት እና ተጠሪነት “ከፌደራል መንግስት ጋር በመነጋገር እንደገና መቃኘት እና መስተካከል ይገባዋል” ብለው ነበር። 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነትን ለከተማ አስተዳደሩ እንዲሆን የማድረግ ሂደት “በጣም የዘገየ ነው” ያሉት ዶ/ር ቀነዓ ያደታ፤ “ችግሩ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው” ሲሉ አስተያየቱን ከሰነዘሩት የምክር ቤት አባል ጋር የተስማማ ምላሽ ሰጥተዋል። ችግሩን በመፍታት ረገድም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን መነሻ ያደረገ ጥናት አጠናቅቆ ለፌደራል መንግስት ማቅረቡን ገልጸዋል።

ለዚህ ጥናት በመጀመሪያ መነሻ የሆኑት የህግ ማዕቀፎችን መሆናቸውን ዶ/ር ቀነዓ ለምክር ቤት አባላቱ አስረድተዋል። በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ተጠሪነትን በተመለከተ በአምስት የህግ ማዕቀፎች ላይ ዳሰሳ መሰራቱን ጠቁመዋል። 

ዳሰሳ የተሰራባቸው የህግ ማዕቀፎች የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብ፣ የፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ፣ የፌደራል ፖሊስ መተዳዳሪያ ደንብ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን አስፈጻሚ አካላት መልሶ ለማደራጀት የተዘጋጀ አዋጅ ናቸው።  

በሰኔ 1989 ዓ.ም. የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ቻርተር፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ተጠሪነትን በግልጽ አያስቀምጥም። ሆኖም በዚሁ ቻርተር የአዲስ አበባ ከተማ ርዕሰ መስተዳድር “የፖሊስ ኃይልን በበላይነት እንደሚመራ” ተደንግጓል። በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፖሊስ የተጀመረ የወንጀል ምርመራ ጉዳይ የፌደራል ወንጀልን የሚመለከት ሆኖ ሲገኝ፤ ለፌደራል ፖሊስ እንዲተላለፍ እንደሚደረግም በዚህ ቻርተር ላይ ተቀምጧል።

የፌደራል ፖሊስን አደረጃጀት እና አስተዳደር ለመወሰን በሰኔ 1992 ዓ.ም. በወጣው አዋጅ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጉዳይ ጭርሱኑ አልተነሳም። ይህ አዋጅ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ጋር ስለሚኖረው የስራ ግንኙነት የሚዳስሱ ክፍሎችን ያካተተ ቢሆንም፤ በፌደራል ስር ያሉት የአዲስ አበባም ሆነ የድሬዳዋ ከተሞችን ጉዳይ የሚመለከቱ አንቀጾችን አልያዘም።

ከሶስት ዓመታት በኋላ በጥር 1995 ዓ.ም. የወጣው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አዋጅ ግን የሁለቱን ከተሞች የፖሊስ ኃይሎች በቀጥታ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን አጽድቋል። ሁለቱ ከተሞች፤ በአዋጁ መሰረት በሚወጣ ደንብ ተወስኖ የሚሰጥ ስልጣን እና ተግባር የሚኖራቸው የፖሊስ ኮሚሽን እንደሚቋቋምላቸው በዚህ አዋጅ ላይ ተቀምጧል። 

የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠሪነት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚሆንም በ1995ቱ አዋጅ በግልጽ ተመልክቷል። የሁለቱ ከተሞች ፖሊስ ኮሚሽኖችን በኮሚሽነርነት የሚመሩ ኃላፊዎች የሚመደቡት “በመንግስት” እንደሆነም አዋጁ ጠቁሟል። የከተሞቹ ፖሊስ ኮሚሽኖች በጀት “አግባብ ባለው አስተዳደር” እንደሚመደብ ይኸው አዋጅ ይገልጻል። የሁለቱ ከተሞች ፖሊስ ኮሚሽኖች ዓመታዊ እቅዳቸውን እና የስራ አፈጻጸማቸውን “ለሚመለከተው አስተዳደር” የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አዋጁ ይደነግጋል። 

ከዚህ አዋጅ መውጣት ሰባት ወር በኋላ የጸደቀው የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ተጠሪነት ጉዳይ ይበልጥ አብራርቶታል። በሐምሌ 1995 ዓ.ም. በፌደራል ፓርላማ የወጣው ይህ አዋጅ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት በዋነኛነት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቢሆንም፤ ተጠሪነቱ በውክልና ለከተማው አስተዳደር ይሆናል ይላል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽነር እና ምክትል ኮሚሽነር አሁን በፈረሰው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እንደሚሾሙ በቻርተሩ ቢጠቀስም፤ የከተማውን ፖሊስ የዕለት ተዕለት ስራ የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ግን ለከተማይቱ ከንቲባ ነበር። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዕቅድ እና በጀት እንዲሁም ዓመታዊና ወቅታዊ የስራ አፈጻጸም የሚቀርበውም ለከተማይቱ ከንቲባ እንደሚሆን በቻርተሩ ተብራርቷል። 

የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር ሌላው የጠቀሰው ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚወጣ ነበር። በዚህ መሰረት የተሻሻለው ቻርተር በጸደቀ በአራተኛው ወር  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የከተማውን ፖሊስ ኮሚሽን የሚያቋቁም ደንብ በጥቅምት 1996 ዓ.ም አውጥቷል። 

በዚህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑ በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል። የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽንን “አደረጃጀት፣ አሰራር፣ ስልጠና፣ ወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራ የሚመለከቱ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ እና የስታንደርዳይዜሽን አቅጣጫዎች” የሚወስነው እና የሚከታተለው የፌደራል ፖሊስ መሆኑም በደንቡ ተዘርዝሯል። 

በዚህ ደንብ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የከተማይቱ ከንቲባ ያላቸው ስልጣን እና ኃላፊነት ተብራርቷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማውን ፖሊስ ኮሚሽን ስምሪት እና የዕለት ተዕለት ስራ የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል። የከተማይቱ ከንቲባ በበኩሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ስራ በበላይነት የመምራት እና የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶታል።

እንደ አዲስ አበባ ቻርተር ሁሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብም፤ የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን ዓመታዊ ዕቅድ፣ በጀት፣ ሪፖርት እና የስራ አፈጻጸምን ተከታሎ ለከተማው ምክር ቤት የማቅረብ ኃላፊነት የሰጠው ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ነው። ይህም ሆኖ ግን ከንቲባው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንን አስተያየት ማካተት ይገባዋል ይላል ደንቡ።

ከዚህ ደንብ መውጣት አንድ ዓመት በኋላ የተካሄደው የ1997ቱ ታሪካዊ ምርጫ፤ በአዲስ አበባ ያልተጠበቀ ውጤት  ይዞ ከመጣ በኋላ ግን በአዋጅም ሆነ በደንብ ተቀምጠው የነበሩ ድንጋጌዎች በአፍታ ተቀያየሩ። በምርጫው የአራት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት የሆነው ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ፤ ከአዲስ አበባ ህዝብ ከፍተኛ ድምጽ ማግኘቱን ተከትሎ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ ያስተላለፉት “መመሪያ” የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን መጻኢ ዕጣ ፈንታ የወሰነ ሆኗል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ምርጫው በተካሄደበት ዕለት ግንቦት 7፤ 1997 ምሽት ባስተላለፉት መመሪያ፤ “የጸጥታ አስከባሪዎች በሙሉ በአንድ ዕዝ ሥር ገብተው ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን” መደረጉን አውጀዋል። አወዛጋቢው የጠቅላይ ሚኒስትሩ “መመሪያ” በፍርድ ቤት ጭምር ክርክር ቢደረግበትም ለውጥ ሳያመጣ ቀርቷል።

ከዚያ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳይ በድጋሚ በአዋጅ ደረጃ የተነሳው በ2004 ዓ.ም. በተሻሻለው በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ነው። የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽኖችን ለይቶ ድንጋጌ ባስቀመጠው የአዋጁ ክፍል ላይ፤ የሁለቱ ፖሊስ ኮሚሽኖች ተጠሪነት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሆነ ሰፍሯል። 

የአዲስ አበባ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ በትላንቱ የከተማይቱ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ባቀረቡት ማብራሪያ “የፌደራል ፖሊስ ማቋቋያ አዋጅ ላይ [ያሉ] የተወሰኑ አንቀጾች ውዥንብር ፈጥረዋል” ብለዋል። ዶ/ር ቀነዓ “በአጠቃላይ የህግ ማዕቀፎቹ አጠቃላይ ንባብ (cumulative reading) የሚያሳየው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ያለምንም ጥያቄ የአዲስ አበባ ከተማ መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ነገር ግን በተግባር ነጠላ አንቀጽ (single article) ተወስዶ ለፌደራል ፖሊስ ተጠሪ እንዲሆን ነው የተደረገው” ሲሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌደራል ፖሊስ እንዲሆን መደረጉን በችግርነት አንስተዋል።  

በዚሁ አንቀጽ ስር ስለበጀት እና ስለ ኮሚሽኑ የስራ ክትትል የቀረቡ ድንጋጌዎችም በቢሮ ኃላፊው ተጠቅሰዋል። በፌደራል ፖሊስ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ “የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደሮች ፖሊስ ኮሚሽኖች፤ ዓመታዊ ዕቅዳቸውንና የሥራ አፈፃፀማቸውን ሪፖርት ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ለየከተሞቻቸው አስተዳደር ያቀርባሉ” ይላል። 

ከዚህ ቀደም ለአዲስ አበባ ከንቲባ ተሰጥቶ የነበረው ስልጣን በዚህ መልኩ በአዋጅ ቢነሳም፤ የከተማው አስተዳደር ምክር ቤት ለከተማው ፖሊስ ኮሚሽን በጀት መመደቡ ግን እንዲቀጥል ተደርጓል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለፌደራል ፖሊስ ሆኖ፤ በጀቱ በከተማ አስተዳደሩ የመመደቡ አካሄድ በተግባር ችግር ማስከተሉን  ዶ/ር ቀነዓ በትላንቱ የምክር ቤት ጉባኤ ላይ አንስተዋል።

“የህግ ማዕቀፎቹ ዳሰሳ የሚያሳየው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለአዲስ አበባ ከተማ መሆን እንዳለበት ነው። ምንም በማያሻማ መንገድ ማለት ነው”

ዶ/ር ቀነዓ ያደታ – የከተማይቱ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ

“አሁን ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነሩም አመራሮቹም፤ በቅንነት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ስለሚሰሩ ያን ያህል የገጠመን ብዙ ችግር የለም” ያሉት ዶ/ር ቀነዓ፤ “ነገር ግን በግለሰቦች ፍቃደኝነት ላይ የሚመሰረት መሆን የለበትም” ሲሉ የህግ ማዕቀፍ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠቁመዋል።  

“የአዲስ አበባ ከተማን ሰላም ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ የፖሊስ ተጠሪነት በጣም ወሳኝ ነው” ያሉት የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ ተጠሪነቱ “በማያሻማ መልኩ” መወሰን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። “የህግ ማዕቀፎቹ ዳሰሳ የሚያሳየው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነት ለአዲስ አበባ ከተማ መሆን እንዳለበት ነው። ምንም በማያሻማ መንገድ ማለት ነው” ሲሉ ከዳሰሳው በኋላ የተገኘውን ውጤት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)