በአዲስ አበባ ከተማ ከመሬት ይዞታ እና ካሳ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችን የሚሰማ ጉባኤ ተቋቋመ

በሃሚድ አወል

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሬት ይዞታ ማስለቀቅ እና ካሳ ጉዳዮች አቤቱታ ሰሚ ጉባኤ አቋቋመ። ጉባኤው ከመሬት ይዞታ መነሳት እና ከካሳ ጋር ተያያዥ የሆኑ አቤቱታዎችን የመስማት ስልጣን አለው። 

ጉባኤው የተቋቋመው ለህዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበት፣ ካሳ የሚከፈልበት እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመስከረም 2012 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ አስገዳጅነት ነው። በዚህ አዋጅ መሰረት የሚሰጥ ውሳኔ ላይ ለሚቀርብ አቤቱታ፤ የክልል መንግስታት እንዲሁም የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አቤቱታ ሰሚ ማቋቋም እንዳለባቸው ተደንግጎ ነበር።   

ከሁለት ዓመት በፊት በወጣው በዚህ አዋጅ መሰረት “የመሬት ይዞታ ማስለቀቂያ ትዕዛዝ የደረሰው ወይም እንዲለቅ ትዕዛዝ በተሰጠበት ንብረት ላይ ‘መብቴ ወይም ጥቅሜ ተነካብኝ’ የሚል ማንኛውም ተነሺ” አቤቱታ ማቅረብ ይችላል። ይግባኝ ባይ በክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ለሚቋቋመው አቤቱታ ሰሚ ጉባኤ፤ አቤቱታውን የሚያቀርበው ትዕዛዙ በደረሰው 30 ቀናት ውስጥ እንደሚሆን በአዋጁ ተገልጿል። 

ዛሬ አርብ የካቲት 4፤ 2014 የሁለተኛ ቀን መደበኛ ስብሰባውን ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፤ በአዋጁ መሰረት መመስረት ያለበትን ይህንን አቤቱታ ሰሚ ጉባኤ የሚያቋቁም ደንብ አጽድቋል። አቤቱታ ሰሚ ጉባኤው፤ አቤቱታ የቀረበበትን ውሳኔ የመሻር፣ የማጽናት ወይም የማሻሻል ስልጣን እንዳለው በደንቡ ተቀምጧል። 

የማቋቋሚያ ደንቡ፤ የአቤቱታ ሰሚ ጉባኤውን አደረጃጀት እና አሰራር የሚያስረዱ ዝርዝሮችን በውስጡ አካትቷል። አቤቱታ አቀራረብን እና አወሳሰንን በተመለከተ፤ ደንቡ “አቤቱታ የቀረበበት መስሪያ ቤት መልስ እንዲሰጥ አቤቱታው ከመጥሪያ ጋር እንዲላክለት ይደረጋል” ይላል። አቤቱታ የቀረበበት መስሪያ ቤት መጥሪያ ደርሶት በቀጠሮው ቀን ቀርቦ መልስ ሳይሰጥ ከቀረ አቤቱታው በሌለበት እንደሚታይም በደንቡ ላይ ተደንግጓል። 

የአቤቱታ ሰሚ ጉባኤው በጠቅላላ አምስት አባላት እንደሚኖሩት የጠቀሰው ደንቡ፤ ከእነርሱ ውስጥ በአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት የሚሾመው የጉባኤው ዋና ሰብሳቢ ብቻ መሆኑን ስለ አደረጃጀቱ በዘረዘረበት ክፍሉ ላይ አመልክቷል። የጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ እና ቀሪዎቹ ሶስት አባላት በከተማይቱ ከንቲባ እንደሚሾሙም በደንቡ ላይ ሰፍሯል።  

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የአቤቱታ ሰሚ ጉባኤ አባላት ሹመት ውስጥ መግባታቸው፤ በከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። አንዲት የምክር ቤት አባል “ጉባኤው ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ እንዲቋቋም ከተፈለገ አባላቱን ለምን በከንቲባዋ መሾም አስፈለገ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። 

ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባልም ተመሳሳይ ሀሳብ ያለው አስተያየት አንጸባርቀዋል። አራቱ አባላት በከንቲባዋ መሾማቸው፤ የአቤቱታ ሰሚ ጉባኤው “ ‘ከአስፈጻሚው አካል በአንጻራዊነት የተወሰነ ነጻ መሆን የለበትም ወይ?’ የሚል ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል። 

እኚሁ የምክር ቤት አባል፤ አቤቱታ ሰሚ ጉባኤው ለሚያደራጃቸው ችሎቶች የሚመረጡ ሰዎች በከንቲባዋ እንደሚሾሙ በደንቡ መደንገጉን ተቃውመዋል። ደንቡ “እንዳስፈላጊነቱ ይደራጃሉ” ሲል የገለጻቸው እነዚህ ችሎቶች፤ እያንዳንዳቸው አምስት አባላት ይኖራቸዋል። ሁሉም የችሎቱ አባላት፤ በአቤቱታ ሰሚ ጉባኤው ሰብሳቢ አቅራቢነት በከንቲባዋ እንደሚሾሙ በደንቡ ላይ ሰፍሯል። 

ዶ/ር ሲሳይ “የችሎቶቹን ሰብሳቢ ከንቲባዋ የሚሾሙ ከሆነ፤ [ችሎቶቹ] ከአስፈጻሚው አካል ነጻ አይሆኑም” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ወርቅነሽ ምትኩ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው “ነጻ እና ገለልተኛ ጉባኤ የምናደራጅ አይመስለኝም” ሲሉ በአቤቱታ ሰሚ ጉባኤው ገለልተኝነት ላይ እምነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል። 

ብዙዎቹን የከተማው ምክር ቤት አባላትን አስተያየቶች እና የተነሱ ሃሳቦች “እንደግብዓት እንወስዳቸዋለን” ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ጽዋዬ ሙሉነህ፤ በጉባኤው “ነጻነት እና ገለልተኝነት” ላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። አቤቱታ ሰሚ ጉባኤው ለከተማይቱ ምክር ቤት ተጠሪ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ “እንደ ተቋም ነው የተቋቋመው። እንደ ተቋም ነው የሚሰራው” ሲሉ መልሰዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት፤ “ ‘ስራ አስፈጻሚው በጉባኤው ላይ ጣልቃ መግባት የለበትም’ የሚል ከሆነ ራሱ ይወስናል” በማለት በምክር ቤት አባላቱ የመወሰን ኃላፊነት እንዳላቸው አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ያነሷቸው አስተያየቶች በደንቡ ውስጥ ከተካተቱ በኋላ እንዲጸድቅ በዛሬው ስብሰባ በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል። በዛሬው ስብሰባ ላይ ከተገኙ 105 የምክር ቤት አባላት ውስጥ፤ ሁለት አባላት ብቻ ድምጽ ከመስጠት ሲታቀቡ ቀሪዎቹ  የደንቡን መጽደቅ ደግፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)