የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ የአገራዊ ምክክሩ ሂደት ለጊዜው ቆሞ በድጋሚ ውይይት እንዲደረግበት ጥያቄ አቀረበ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገራዊ ምክክር ሂደት ለጊዜው “ገታ ተደርጎ” በአጠቃላይ አካሄዱ ላይ በድጋሚ ውይይት እንዲደረግ ጥያቄ አቀረበ። ምክር ቤቱ ይህንን ጥያቄውን ያቀረበው፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና ለአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባስገባው ደብዳቤ ነው። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ለሁለቱ ጽህፈት ቤቶች ደብዳቤውን የላከው፤ አገራዊ ምክክር ሂደቱን በተመለከተ በጠቅላላ ጉባኤ ደረጃ ግምገማ ካካሄደ በኋላ መሆኑን የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 3፤ 2014 በተካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤ የምክር ቤቱ አባል የሆኑ 45 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል። 

ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ መጠናቀቅ በኋላ የጋራ ምክር ቤቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ባስገባው ደብዳቤ፤ አገራዊ ምክከሩ ግልጽ እና አካታች ይሆን ዘንድ አሁን የተጀመረው የምክክር ሂደት “ለጊዜው እንዲገታ” መጠየቁን ዶ/ር ራሄል ገልጸዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥም፤ ወደ ዋናው ምክክር ከመገባቱ በፊት ምክር ቤቱ “ምላሽ ሊያገኙ ይገባቸው ነበር” ባላቸው ጉዳዮች ላይ በድጋሚ ውይይት እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡንም ሰብሳቢዋ አክለዋል። 

“አሁን ያለው ነገር ከመነሻው ላይ መስተካከል ስላለበት፤ እንደገና ዳግም ተዓማኒ ሆኖ መነሳት ስላለበት፣ [ችግሮችን] በአግባቡ እየፈታን ሄደን በአካታችነቱ እንድንዘልቅ፣ አሁን ፓርላማው እየሄደበት ያለበትን ሁኔታ ቆም አድርጎ ወደ ምክክሩ እንመለስ [ብለናል]” ሲሉ ዶ/ር ራሄል ምክር ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሚያቋቋም አዋጅ ያጸደቀው ባለፈው ታህሳስ ወር ነው። የአዋጁን መጽደቅ ተከትሎ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችን ጥቆማ ሲቀበል ቆይቷል። ሁለት ሳምንት ገደማ በፈጀው የጥቆማ መቀበያ ጊዜ የ632 ግለሰቦች ዝርዝር ለጽህፈት ቤቱ መቅረቡ ተገልጿል። 

የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤቱ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶችን በመጠቀም፤ ከተጠቆሙ ግለሰቦች ውስጥ አርባ ሁለቱን በዕጩ ኮሚሽነርነት መምረጡን ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ አስታውቋል። የዕጩ ኮሚሽነሮች አመራረጥ ሂደቱ “አሳታፊ አልነበረም” የሚሉት ዶ/ር ራሄል፤ ከባለድርሻ አካላት የተሰጡ “ግብዓቶችን አለማካተቱ” ሌላው በችግርነት የሚጠቀስ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል። 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አዋጅ ከመጽደቁ በፊት፤ የፍትህ ሚኒስቴር በአዋጁ ረቂቅ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባካሄደው ውይይት የተሰጡ ግብዓቶች በተገቢው መንገድ አለመካተታቸውን ለዚህ በአስረጂነት ይጠቅሳሉ። “ብዙ ያልተካተቱ ግብዓቶች ስላሉ [አዋጁን] ወደ ማጽደቁ እንዳይሄድ፤ እንደገና ወደ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተመልሶ ‘በደንብ ሊመከርበት ይገባል’ የሚል ደብዳቤ ጽፈን ጠይቀን ነበር” ሲሉም ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በኩል የተደረገውን ጥረት ያስረዳሉ።     

የጋራ ምክር ቤቱ ይህንን ደብዳቤ የጻፈው ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ቢሮ እና ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እንደነበር ሰብሳቢዋ ያስታውሳሉ። ሆኖም ለደብዳቤው ተገቢው “ትኩረት አልተሰጠውም” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

ዶ/ር ራሄል ሌላው በመሰረታዊ ችግርነት የሚጠቅሱት ጉዳይ፤ አርባ ሁለቱ ዕጩ ኮሚሽነሮች የተመረጡበት መስፈርት “ግልጽ አለመሆኑን” ነው። ከመነሻው ጀምሮ የተጠቆሙት ሁሉም ዕጩዎች “ለህዝብ ይፋ መደረግ ነበረባቸው” የሚል አቋም ያላቸው ዶ/ር ራሄል፤ ይህ ቢደረግ ኖሮ በስተኋላ የተስተዋለው “መስፈርቱን የማያሟሉ” ግለሰቦች ለዕጩ ለኮሚሽነርነት የመቅረብ ችግርን ያስቀር እንደነበር ያብራራሉ።  

የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢዋ በችግርነት የሚጠቅሱት ጉዳይ “ከዕጩ ኮሚሽነሮች መካከል በአዋጁ የተቀመጡትን መስፈርት የማያሟሉ አሉበት” የሚል ነው። በዕጩ ኮሚሽነርነት ስማቸው ከተዘረዘሩት ውስጥ “የሁለት ሀገር ዜግነትን የያዙ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ያላቸው እና በወንጀል ተከስሰው የሚያውቁ ተካትተውበታል” ሲሉ ዶ/ር ራሄል ይወነጅላሉ። 

በአገራዊ ምክከር ኮሚሽን መቋቋያ አዋጅ መሰረት ለኮሚሽነርነት ከሚያበቁ ዘጠኝ መስፈርቶች መካከል በቀዳሚነት የተቀመጠው፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው መሆን ነው። ኮሚሽነር ሆነው የሚሾሙ ግለሰቦች “የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ” እና “በወንጀል ተከስሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያልተላለፈባቸው” ሊሆኑ እንደሚገባ በአዋጁ ሰፍሯል። በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት የሚያገለግሉ 11 ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩ በአዋጁ ተደንጓል።

በኮሚሽነሮች አመራረጥ እና በአጠቃላይ የምክክር ሂደቱ ላይ ጥያቄ ያቀረበው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ ገዢው ፓርቲን ጨምሮ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ ነው። የጋራ ምክር ቤቱ ለፓርላማ ያስገባው ደብዳቤ ምላሽ ካላገኘ በቀጣይነት ምን ሊያደርግ እንዳቀደ ጥያቄ የቀረበላቸው ሰብሳቢዋ፤ “ጥያቄያችን መልስ እንደሚያገኝ ነው የምናስበው። ምክንያቱም የእኛ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ጉዳይ ስለሆነ። ጥያቄያችንን ካልተቀበሉ ግን ወደ ህዝባችን ነው የምንመጣው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)