የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አነሳ

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጻሚነት ጊዜ እንዲያጥር የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። የፍትህ አካላት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የጀመሯቸውን ጉዳዮች በመደበኛው የፍትህ አሰጣጥ ስርዓት እንዲያጠናቅቁም ምክር ቤቱ ወስኗል።

ምክር ቤቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ያጸደቀው ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 8 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ነው። በዛሬው ስብሰባ ላይ ከተገኙ 312 የምክር ቤት አባላት ውስጥ 63 የፓርላማ አባላት የአዋጁን መነሳት ተቃውመዋል። ሃያ አንድ የምክር ቤት አባላት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜ ማጠርን በተመለከተ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ሶስት ነጥቦችን የያዘ ነበር። የመጀመሪያው የውሳኔ ሀሳብ “የሀገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው አዋጅ የተፈጻሚነት ጊዜ ከዛሬ የካቲት 8፤ 2014 ቀሪ እንዲሆን ተወስኗል” የሚል ነው።

ሁለተኛው የውሳኔ ሃሳብ “የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያላጠናቀቃቸው ጅምር ስራዎች ካሉ ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ዕለት አንስቶ በሚቆጠር የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲያደርግ” ቀነ ገደብ የሚያስቀመጥ ነው። የፍትህ አካላትን የሚመለከተው ሶስተኛው የውሳኔ ሃሳብ፤ “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የጀመሯቸውን ጉዳዮች በመደበኛው የፍትህ አሰጣጥ ስርዓት እንዲያጠናቅቁ” ዕድል የሚሰጥ ነው። 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ  በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና የዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች ላይ ጫናዎች ማስከተሉን እና የቱሪዝም ዘርፉንም መጉዳቱን ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። “የአዋጁ መቀጠል በዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ ከሚኖረው ከፍተኛ ጫና በተጨማሪ ሌሎች ዘርፈ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳቶች ስላሉት፤ የጸጥታው ሁኔታ የተሻሻለ እስከሆነ ድረስ አዋጁን ባለበት ማስቀጠሉ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ሲሉም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የተወሰነበትን ምክንያት አብራርተዋል።

በዛሬው ስብሰባ አስተያየት ከሰጡ 10 የፓርላማ መካከል አምስቱ አዋጁ “በፍጹም ሊነሳ አይገባም” ሲሉ ጠንካራ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ተቃውሞ ያቀረቡ የፓርላማ አባላት በተደጋጋሚ ያነሱት መከራከሪያ በአፋር ክልልና የአማራ ክልልን ከትግራይ በሚያዋስኑ ቦታዎች አለ ያሉትን “ጦርነት” ነው። እነዚሁ የምክር ቤት አባላት “ከጦርነቱ” በተጨምሪ በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሉ “የጸጥታ ስጋቶች” ባልተቀረፉበት ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ አይገባም ሲሉ ተሟግተዋል።

አቶ መስፍን እርካቤ የተባሉ የምክር ቤት “[አዋጁን] አሁን ለማንሳት ምንድን ነው ያስቸኮለው?” ሲሉ  አስተያየታቸውን በጥያቄ ጀምረዋል። ህወሓት አምስት የአፋር ክልል ወረዳዎችን “መውረሩን” በመጥቀስ “ጦርነት ላይ ነው ያለነው” ሲሉም ለምክር ቤቱ አስረድተዋል። የፓርላማ አባሉ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ “የጸጥታ ስጋቶችን” በማንሳት፤ “ይህ በሆነበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት ምን የሚያጣድፍ ነገር አለ? የበለጠ ማጠናከር አይቻልም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ ምክንያት የሆነውን ስጋት በተመለከተ በፓርላማው የመንግስት ዋና ተጠሪ የቀረበው ማብራሪያም አቶ መስፍንን አላሳመናቸውም። “አቶ ተስፋዬ [በልጅጌ] ‘በመደበኛ የህግ ስርዓቱ ስጋቶችን መከላከል የሚቻልበት ሁኔታ አለ’ ብለዋል። ይሄ ቢሆን ጥሩ ነው። እኔ [ግን] አይመስለኝም” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባይነሳ፣ ቢቆይ እና ቢራዘም ይሻላል የሚል ሃሳብ አለኝ” ሲሉ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት በጽኑ ተቃውመው አስተያየት ከሰጡ የምክር ቤት አባላት መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ይገኙበታል። ዶ/ር ደሳለኝ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት አስፈላጊ አድርጎት የነበረው ሁኔታ ጉልህ በሆነ መልኩ ተቀይሯል” መባሉን ተቃውመዋል። የአብን አመራሩ “ጉልህ በሆነ ሁኔታ የተቀየረው አንድ ነገር ብቻ ነው የሚታየኝ እንጂ ሶስት ወይም አራት ነገሮች አልተቀየሩም” ሲሉ ተሟግተዋል።

ዶ/ር ደሳለኝ የተቀየረው ነገር የህወሓት ኃይሎች ተቆጣጥረዋቸው ከነበሩት አካባቢዎች መውጣታቸው መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ሌሎች ሁኔታዎች እንዳሉ ናቸው ብለዋል። “የመጀመሪያው የህወሓት የማድረግ አቅም (Military capability) ነው። አሁንም ለጦርነት እየተዘጋጀ እና የጦር ነጋሪት እየጎሰመ ባለበት ሁኔታ ይሄ ነገር አልተቀየረም። ሁለተኛው የህወሓት እብሪት እና ጠብ አጫሪነት አሁንም አልተቀየረም” ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዩ መከራከሪያቸውን ለምክር ቤቱ አሰምተዋል።

 “ገና [ለገና] የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ለማስደስት እና የተወሰነ የገጽታ መሻሻል ለማምጣት ተብሎ መንግስት የዜጎችን የህይወት እና ንብረት ደህንነት ዋስትና ባልሰጠበት ሁኔታ፤ [አዋጁን] ለማንሳት መቸኮላችን ተገቢ ነው ወይ?” የሚል ጥያቄም ከአብኑ አመራር ቀርቧል። 

ዶ/ር ሀንጋሳ አህመድ የተባሉ የፓርላማ አባል በበኩላቸው የኦሮሚያ ክልልን በአስረጂነት በማንሳት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በጽኑ ተቃውመዋል። “ለኦሮሚያ ክልል ራሱ አዋጅ  ያስፈልገዋል። ለክልሉ ብቻ” ያሉት ዶ/ር ሀንጋሳ፤ “396 ገደማ የገጠር ከተሞች እና መንደሮች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ተይዘዋል። ኦነግ ሸኔ ዛሬ ግብር እየሰበሰበ ነው” ሲሉ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው በተመረጡበት ክልል ያለውን ሁኔታ ለፓርላማው አስረድተዋል።

“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” የሚሉት ዶ/ር ሀንጋሳ፤ “የምክር ቤት አባላት ከፓርቲ ወጣ ብለን አይተን ለህሊናችን፣ ለህግ እና ለህዝባችን ስንል ይኼንን [የውሳኔ ሃሳብ] ብንቃወም ደስ ይለኛል” ሲሉ ሌሎች የፓርላማ አባላት ከጎናቸው ይሆኑ ዘንድ ጠይቀዋል። 

ከጸጥታ ስጋቶች በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለው መርማሪ ቦርድ፤ ሪፖርት አለማቅረቡን በመጥቀስ አዋጁ እንዳይነሳ የተቃወሙ የፓርላማ አባላት ነበሩ። አንድ የምክር ቤት አባል “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እስካሁን ስለሄደበት ርቀት በአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ ቢነሳ አይሻልም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። የፓርላማ አባሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርዱ ለምን ሪፖርት አላቀረበም ሲሉም ጠይቀዋል። 

ዶ/ር ተውፊቅ አብዱላሂ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባልም በተመሳሳይ “በቅድሚያ መርማሪ ቦርዱ ሪፖርቱን ማቅረብ ነበረበት” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። ዶ/ር ሀንጋሳ በበኩላቸው “መርማሪ ቦርዱ ሪፖርቱን አቅርቦ፤ እሱ ላይ ተወያይተን፣ ያለውን ለውጥ በመርማሪ ቦርድ የታየውን አይተን፤ ለሀገራችን፣ ለህዝባችን ይጠቅማል የሚለውን ውሳኔ በሚቀጥለው ብንወስን መልካም ነው” ሲሉ አዋጁ ሊነሳበት ይገባ ነበር ያሉትን ሂደት አቅርበዋል። 

የአዋጁ መነሳት ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመውን ያህል በሌሎች የምክር ቤት አባላትም ድጋፍን አግኝቷል። ድጋፉን ከሰጡት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤ “ከጅምሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጀ መታወጅ የለበትም ነበር” የሚል አቋማቸውን በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አንጸባርቀዋል። 

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር አሸብር “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለኢትዮጵያ ያስከተለው ትልቅ ፈተና ነው። ገጽታችንን ነው ሙሉ በሙሉ ያጠፋው” ሲሉ አዋጁ አስከተለ ያሉትን “ችግር” ገልጸዋል። “ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለኢትዮጵያ ምንድን ነው የጠቀመው?” የሚል ጥያቄ የሰነዘሩት ዶ/ር አሸብር “ማንኛውንም ነገር በመደበኛው የህግ ስርዓት ውስጥ ሆነን ማሳለፍ እንችል ነበር” ሲሉ ቀድሞም ቢሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጅ አልነበረበትም የሚለው ሃሳባቸውን አስተጋብተዋል።

በኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው “የሃገርን ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል” በሚል ነበር። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሶስት ሳምንት በፊት ጥር 18፤ 2014 ባካሄደው ስብስባ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜ እንዲያጥር የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ማጽደቁ ይታወሳል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁ እንዲነሳ የወሰነው፤ አዋጁን ማውጣት “የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ” መሆኑን በወቅቱ አስታውቆ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃዎች ከቆይታ በኋላ ተካተውበታል]