በተስፋለም ወልደየስ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር የጋዜጠኞች በተደጋጋሚ እየታሰሩ መፈታት “እየተባባሰ” መጥቷል አለ። ጋዜጠኞች “ሙያዊ ነጻነታቸውን ሳያጡ እንዲሰሩ ሊፈቅድላቸው” እንደሚገባ የገለጸው ማህበሩ፤ በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰው “ተደጋጋሚ እስር እና ማንገላታት” እንዲቆም አሳስቧል።
ማህበሩ ማሳሰቢያውን የሰጠው “ለዜጎች መብት መከበር የሚሟገተው ጋዜጠኛ መብት ይከበር” በሚል ርዕስ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 8፤ 2014 ባወጣው መግለጫ ነው። በኢትዮጵያ ያለው የፕሬስ ነጻነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሻሻል አሳይቶ እንደነበር የጠቆመው ማህበሩ፤ ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይህ በጎ ጅምር “እየተሸረሸረ መሄዱን” አስታውቋል።
ለዚህ ማሳያነትም በ11 የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የደረሱ እስራቶችን ዘርዝሯል። በማህበሩ መግለጫ ለአብነት ከተጠቀሱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ውስጥ ሶስቱ አሁንም በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ፤ የፌደራል ፖሊስ “የአሸባሪውን ሸኔ ቡድንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ስራ ሲሰሩ ነበር” በሚል በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ናቸው።
ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሶስት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ውስጥ፤ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኛ የሆነው አዲሱ ሙሉነህ ከአንድ ወር ተኩል እስር በኋላ መለቀቁን የማህበሩ መግለጫ ጠቁሟል። የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያ ቶማስ እንግዳ ግን አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ማህበሩ አመልክቷል።
“በተጠርጣሪነት የተያዙት ጋዜጠኞች ወንጀለኛነታቸው በፍርድ ቤት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሚደነግገው ውጭ አስቀድሞ እንደወንጀለኛ እንዲቆጠሩ በማድረግ ምስላቸው በሚዲያ እንዲሰራጭ በማድረግ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ተፈጽሞባቸዋል” ሲል ማህበሩ በዛሬው መግለጫው ድርጊቱን ኮንኗል።
ታህሳስ 1፤ 2014 ከመኖሪያ ቤት በፖሊስ ከተወሰደ በኋላ እስካሁንም በእስር ላይ የሚገኘው “ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ጉዳይም በማህበሩ መግለጫ ተነስቷል። “ታምራት ነገራ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እስካሁን በእስር ላይ መቆየቱ እጅግ አሳዛኝ እና ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን ማህበራችን ያምናል” ሲል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበሩ አቋሙን አስታውቋል።
“ጋዜጠኞችን ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ እንዲሁም ይህንን ያህል ጊዜ እስር ቤት ማቆየት ከሕግም ከሞራልም ያፈነገጠ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ ግን ይህ ጉዳይ የተለመደ ሆኗል” ሲል ማህበሩ “እየተባባሰ መጥቷል” ያለውን የጋዜጠኞች እስራት ጉዳይ አጽንኦት ሰጥቷል። መንግስት ጋዜጠኞችን መጠየቅና ማብራሪያ ማግኘት ሲፈልግ፤ በሀገሪቱ ህግ እንዲሁም ሀገሪቱ በተቀበለቻቸው ዓለም ዓቀፋዊ ስምምነቶች መሰረት የተፈራረመቻቸውን መብቶች ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ማህበሩ አሳስቧል።
“አጥፊ ግለሰቦችና ባለሙያዎች ሲኖሩ በህግ አግባብ እንደማንኛውም ዜጋ ሊጠየቁ ይገባል። ይህ ሲሆን ግን ፈጸሙት በተባለው ድርጊት በሕግ አግባብ ብቻ የሚጠየቁበት አግባብ ተከብሮ፣ በትክክለኛው ጊዜ ክስ ተመስርቶባቸው፣ በሕግ ጥላ ስር ባረፉበት ቦታ በቤተሰቦቻቸው የመጠየቅ መብታቸው ተከብሮላቸው ሊሆን ይገባል” ብሏል የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)