በሃሚድ አወል
በፌደራል ስር የነበረው የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ የትራንስፖርት ተቋማት ተጠሪነት፤ ለየከተሞቹ አስተዳደር ሊሰጥ ነው። ተቋማቱ ተጠሪነታቸው ተስተካክሎ፣ ራሳቸውን ችለው በአዲስ መልክ እንዲደራጁ የሚያደርግ የአዋጅ ረቂቅ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 8 ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል።
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች የትራንስፖርት ተቋማት፤ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሆነው እንዲሰሩ በአዋጅ የተወሰነው በ1997 ዓ.ም ነው። የከተሞቹ የትራንስፖርት ተቋማት ወደ ፌደራል ስር እንዲሆን የተደረገው፤ በዚያው ዓመት ግንቦት ወር ተደርጎ በነበረው አጠቃላይ ምርጫ ተቃዋሚው የቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ በመመረጡ ነበር።
የምርጫ ዘመኑን በሰኔ 1997 ዓ.ም ያጠናቀቀው ሁለተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የተቋማቱን ጉዳይ የሚመለከተውን አዋጅ ያጸደቀው፤ ፓርላማው ከተበተነ ከወር በኋላ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ነው። ይህ አዋጅ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የትራንስፖርት ተቋማትን መብት እና ግዴታዎች፤ በወቅቱ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ስር ለነበረው ለትራንስፖርት ባለስልጣን አስተላልፏል።
ከ16 ዓመት ከመንፈቅ ቆይታ በኋላ ተሻሽሎ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው “የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ”፤ በፌደራል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ደረጃ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት የሁለቱ ከተሞች የትራንስፖርት ተቋማት መብት እና ግዴታ እንደ አዲስ ለሚደራጁት ተቋማት የሚተላለፉ መሆኑን አስታውቋል። በአዋጅ ረቂቁ መሰረት፤ በትራንስፖርት ባለስልጣንነት ሲሰራ የቆየው የአዲስ አበባው ተቋም እና የድሬዳዋ ከተማ የትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ተጠሪነት ለየከተማ መስተዳድሮቻቸው ይሆናል።
ይህ ማሻሻያ የተደረገው “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ቻርተር በተሰጠው ስልጣን እና ኃላፊነት መሰረት የትራንስፖርቱን ዘርፍ የሚመራ ተቋም በመዘርጋቱና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርም በተመሳሳይ ሁኔታ ሊሰራ ስለሚችል” እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።
ከአምስት ወራት ገደማ በፊት በመስከረም 2014 የምስረታ ጉባኤውን ያካሄደው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፤ የከተማይቱን የትራንስፖርት ቢሮ በአዋጅ ማደራጀቱ ይታወሳል። የትራንስፖርት ቢሮውን በኃላፊነት እንዲመሩ በወቅቱ የተሾሙት አቶ ዳዊት የሺጥላ፤ በአደረጃጀቱ መሰረት የከተማይቱ ካቢኔ አባል ሆነዋል።
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞችን የትራንስፖርት ተቋማት አደረጃጀት የሚቀይረው የተሻሻለው “የመንገድ ትራንስፖርት አዋጅ”፤ በተወካዮች ምክር ቤት የከተማ መሠረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲታይ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ተመርቷል። የአዋጅ ረቂቁ ለዝርዝር ዕይታ የተመራው በአንድ የምክር ቤት አባል ድምጸ ተዐቅቦ ነው። በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ 312 የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገኝተዋል።
የሁለቱ ከተሞች የትራንስፖርት ተቋማት ተጠሪነት ለከተሞቹ የሚተላለፉበትን ሂደት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት፤ ለትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አላገኘንም። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አመራሮችም “ስብሰባ ላይ ነን” በማለታቸው የከተማ አስተዳደሩን መረጃ ማካተት አልቻልንም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)