ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 26 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በአንድ ወር እንዲያካሄዱ ቀነ ገደብ ተሰጣቸው

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 26 ሀገራዊ እና ክልላዊ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ ቀነ ገደብ አስቀመጠ። ቦርዱ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ ማሳሰቢያ ከሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ይገኙበታል።

ምርጫ ቦርድ ባለፈው ህዳር ወር ከፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ሁሉም ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ይህንኑ ውሳኔውን በመመርኮዝ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 9 ባወጣው ማስታወቂያ፤ 26ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ እና የሰነድ ማሻሻያዎችን አድርገው ለቦርዱ እንዲያስገቡ አሳስቧል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ቢያንስ በሶስት ዓመት አንድ ጊዜ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ይደነግጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ማካሄድ ከሚገባቸው ጊዜ በሶስት ወራት የዘገዩ ከሆነ እና ከዚህ በኋላ ቦርዱ በሚሰጠው የጊዜ ገደብ ጉባኤውን ሳይካሄዱ የቀሩ ከሆነ ከምዝገባ ሊሰረዙ እንደሚችሉ በአዋጁ ተቀምጧል።

ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያካሄዱ በመጀመሪያ የወሰነው ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ነበር። ከምርጫው በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ያደረጉት ሁለት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ) ናቸው።

ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ ቀነ ገደብ ከተቀመጠላቸው 13 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ይገኙበታል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ካለባቸው ክልላዊ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ፤ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) እና ዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲ ሉዓላዊነት (ዓረና) ተካትተዋል።

ምርጫ ቦርድ ማሳሰቢያውን ከሰጣቸው ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በመጪው መጋቢት ወር ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሄድ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስታውቋል። የአብን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ካካሄደው ጉባኤ በኋላ ባወጣው መግለጫ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ከአንድ ወር በኋላ መጋቢት 11፤ 2014 እንዲካሄድ መወሰኑን ገልጿል።

ከ26ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተው ክልላዊው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ፤ በተያዘው የካቲት ወር ጠቅላላ ጉባኤውን እንደሚያካሄድ አስታውቆ ነበር። የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ እስክንድር ነጋ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ባለፈው በጥር ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት መግለጫ፤ ጠቅላላ ጉባኤው ባልደራስን ሀገር አቀፍ ፓርቲ ሊያደርገው እንደሚችል ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)