በተስፋለም ወልደየስ
በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት ለማስመጣት የሚደረገው ጥረት “በወቅታዊ ሁኔታዎች” ምክንያት መዘግየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቃባይ ዲና ሙፍቲ ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን የመመለስ “ግዴታም፤ ኃላፊነትም ስላለበት” በዚያ አቅጣጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዲና ሙፍቲ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 10 በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት፤ አሁን በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ ለሚገኙ ዜጎች “የመጨረሻ መፍትሔ” ተደርጎ እየተሰራ ያለው እነርሱን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ብሔራዊ ኮሚቴ መስርቶ የ“ቴክኒካል” ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በእስር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለማምጣት በመንግስት በኩል ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ቃል አቃባዩ ቢናገሩም፤ ሂደቱ ላይ ግን የመዘግየት ጥያቄ ሊነሳበት እንደሚችል አምነዋል። ዲና “በአንዳንድ ወቅታዊ ሁኔታዎች ሊዘገይ ይችላል። ነገር ግን የመጨረሻ መፍትሔው ዜጎችን ማምጣት ነው” ቢሉም፤ “ወቅታዊ ሁኔታዎች” ያሏቸውን ጉዳዮች ሳያብራሩ ቀርተዋል።
ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት በማምጣት ረገድ፤ በሳዑዲ አረቢያ በኩልም ያለው አቋም “ኑ ውሰዷቸው፤ መልሷቸው” የሚል መሆኑን ቃል አቃባዩ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስ ግን “አያያዛቸው እንዲሻሻል እና ጉዳት እንዳይደርስባቸው” ከሚመለከታቸው ሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት ጋር ምክክር መደረጉንም ተናግረዋል።
ምክክሩን ያደረገው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ሀገሪቱ ተጉዞ የነበረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን መሆኑንም ጠቁመዋል። በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ የተመራው ይህ የልዑካን ቡድን በሳዑዲ አረቢያ ቆይታው፤ በተለያየ ደረጃ ካሉ የሀገሪቱ መንግስት አመራሮች እና ከሃይማኖት ሰዎች ጋር ጭምር መነጋገሩንም ዲና አብራርተዋል።
በውይይቶቹ ላይ፤ በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚደርሰው “ስቃይ” የሁለቱን ሀገራት “ግንኙነት አይመጥንም” የሚል ነጥብ መነሳቱንም ቃል አቃባዩ አስረድተዋል። ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያለውን “ግንኙነት” በተመለከተ በጋዜጠኞች ጥያቄ ተነስቶላቸው የነበሩት ዲና፤ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ “መነጋገር ይቻላል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከሳዑዲ አረቢያ ስትመልስ የአሁኑ የመጀመሪያዋ አለመሆኑን የገለጹት ቃል አቃባዩ፤ ከዓመታት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ እርሳቸው ራሳቸው ተሳትፈውበት የነበረውን የዜጎችን የማስመለስ ሂደትን አስታውሰዋል። አሁንም በተመሳሳይ መልኩ ሂደቱ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ ከሳዑዲ አረቢያ እንዲመለሱ የተደረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ወደ 90 ሺህ የሚጠጋ እንደነበር ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት መረጃ ያሳያል። ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በገፍ በተመለሱበት በ2006 ዓ.ም የመጀመሪያ ወራቶች ውስጥ ደግሞ፤ ወደ 200 ሺህ ዜጎች ወደ ሀገራቸው ገብተው እንደነበር በመረጃው ተመላክቷል።
በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ በማህበራዊ የትስስር ድረ ገጾች ተከታታይ ዘመቻዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ተመሳሳይ መልዕክት ያዘሉ መግለጫዎችን በማውጣት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ሲያሳስቡ ነበር። ከፓርቲዎቹ አንዱ የሆነው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በሳዑዲ አረቢያ “በጅምላ እስር ቤት ታጉረው ያሉበት ሰቆቃ እጅግ ያሳቅቃል” ብሎ ነበር።
“ብዙ ነገሮች ለተወሰኑ ጊዜያት ቀርተውብን መንግስት የእነዚህን ወገኖቻችንን ሕይወት ቢታደግ የተሻለ ነው” የሚሉ በርካታ ወገኖች እንዳሉ በመግለጫው የጠቀሰው ኦፌኮ፤ ፓርቲው ይህንን ሃሳብ እንደሚደግፍ አስታውቋል። ከሞት ተርፈው በእስር ላይ የሚገኙ ቀሪ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት ለማትረፍ መንግስት “አስቸኳይ እርምጃ” እንዲወስድም ኦፌኮ ተማጽዕኖውን አቅርቦ ነበር።
ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) በበኩሉ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ በሳዑዲ አረቢያ በእስር ቤት እና ማጎሪያ ካምፖች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እንዲለቀቁ ጠይቋል። ይህንኑ ጥያቄ የያዘ ደብዳቤ የዚያኑ ዕለት በአዲስ አበባ ለሚገኘው የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ ማስገባቱንም ፓርቲው አስታውቋል። ፓርቲው በዚሁ ደብዳቤው “እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ በእስር ቤት እና ማቆያ ካምፖች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ተለቅቀው ወደ ሀገራቸው መምጣት የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው” ጥያቄ ማቅረቡ ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)