በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 149 የቤህነን አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ ምርጫ ቦርድ ገለጸ

በሃሚድ አወል

በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ 149 የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ (ቤህነን) አባላት በእስር ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ሃያ ሁለት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላትም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት በፌደራል እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ቦርዱ ገልጿል። 

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር ዛሬ ሐሙስ የካቲት 10፤ 2014 በአዲስ አበባው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ባደረገው ውይይት ላይ ነው። በኢትዮጵያ ባለፈው ጥቅምት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ በኋላ፤ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸው እንደታሰሩባቸው ለምርጫ ቦርድ አቤቱታቸውን አቅርበው ነበር። 

ለቦርዱ አቤት ካሉ ፓርቲዎች ውስጥ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው እና ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር በክልሉ በከፊል በተካሄደው ምርጫ የተሳተፈው ቤህነን ይገኝበታል። ምርጫ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ ማጣራት ሲጀምር በእስር ላይ የነበሩ የቤህነን አባላት 492 እንደነበሩ፤ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ምርጫ ቦርድ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ጋር ካደረገው ተደጋጋሚ ውይይት በኋላ 280 የቤህነን አባላት ቢፈቱም፤ 149 የንቅናቄው አባላት ግን አሁንም በእስር ላይ መሆናቸው ታውቋል። በርካታ የፓርቲው አባላት ታስረው የሚገኙት፤ በአሶሳ ዞን ስር በሚገኙት ሸርቆሌ እና ኩርሙክ ወረዳዎች እንደሆነ በዛሬው ስብሰባው ላይ ተገልጿል።

በሸርቆሌ ወረዳ የታሰሩ የቤህነን አባላት በ50 መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ውብሸት፤ በኩርሙክ ወረዳም 47 የፓርቲው አባላት በተመሳሳይ ሁኔታ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዳሉ አስረድተዋል። በአሶሳ፣ ባምቢሲ፣ መንጌ እና ኦዳ ቡልዱጉል ወረዳዎችም ሌሎች የፓርቲው አባላት ታስረው እንደሚገኙ የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አብራርተዋል።  

በዛሬው የምርጫ ቦርድ ስብሰባ ላይ የተገኙት የቤህነን የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መርቀኔ አዙቤር፤ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በቁጥጥር ስር ያሉት አብዛኞቹ የፓርቲው አባላት እስካሁን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ገልጸዋል። በእስር ላይ ካሉት 149 የቤህነን አባላት መካከል አንድ ሰው ላይ ብቻ ክስ መመስረቱን የገለጹት አቶ መርቀኔ፤ ነገር ግን በክልሉ መንግስት ሲቀርብ የነበረው ግን ሁሉም ክስ እንደተመሰረተባቸው ነው ብለዋል። 

“ከጥቅምት ጀምሮ እስካሁን ድረስ እስር ላይ ያሉት፤ በምንም አይነት ክስ ያልቀረበባቸው ሰዎች ናቸው። ክስ የሚመሰረትባቸው ሰዎች ካሉ ወደ ፍትህ መሄድ አለባቸው የሚል አቋም አለን። አለበለዚያ ግን ከእስር መፈታት አለባቸው የሚል እምነት ነው ያለን” ሲሉ የቤህነን የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ የፓርቲያቸውን አቋም አስታውቀዋል።  

ከቤህነን አባላት በተጨማሪ በአዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች ታስረው የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ጉዳይም በዛሬው ስብስባ ላይ ተነስቷል። በእስር ላይ ከሚገኙ 22 የኦነግ አባላት ውስጥ ሰባቱን በቁጥጥሩ ስር ያደረገው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መሆኑን የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ተናግረዋል።  

የቦርዱ አባላት እነዚህን የኦነግ አባላት በታሰሩበት ቦታ በመሄድ እንደጎበኟቸው የገለጹት አቶ ውብሸት፤ ታሳሪዎቹ “ከሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በጥቆማ የተያዙ” መሆናቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹን አስረድተዋል። በሰባቱም ላይ እስካሁን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው ምክትል ሰብሳቢው አክለዋል።

ከእነዚህ የኦነግ አባላት በተጨማሪ፤ ሌሎች ስምንት የግንባሩ አባላት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት፣ አራት አባላት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት፣ ቀሪ ሶስቱ ደግሞ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚገኙ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አብራርተዋል። ምርጫ ቦርድ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቤቱታዎችን እንደሚያጣራ ባስታወቀበት ወቅት በርካታ ቅሬታ የቀረበው በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ገልጾ ነበር። 

በአዲስ አበባ አባላቶቻቸው እንደታሰሩባቸው አቤቱታ ያቀረቡት ፓርቲዎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ነበሩ። በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር ከነበሩ 23 የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል ሃያ አንዱ መፈታታቸውን የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሰለሞን ታፈሰ እስካሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ አቶ ውብሸት ጨምረው ገልጸዋል። ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ሊቀመንበር ጉዳይ ሲከታተል የቆየ ቢሆንም በስተመጨረሻ “ክስ ይመሰረትባቸዋል” የሚል ምላሽ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማግኘቱን የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)