በኢትዮጵያ ታስረው የነበሩ 16 ሰራተኞቹ ሙሉ በሙሉ መፈታታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አስታወቀ። የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቃባይ ስቴፈን ዱጃሪች፤ የሰራተኞቹን መፈታት ትላንት አርብ ምሽት በኒውዮርክ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጠዋል።
ዱጃሪች በዚሁ መግለጫቸው በኢትዮጵያ “ባለስልጣናት ታስሮ የነበረው የመጨረሻው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ ከእስር ተፈቷል” ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 16 ሰራተኞቹ በኢትዮጵያ መንግስት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ይፋ ያደረገው ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ነበር።

ተመድ ሠራተኞቹ በኢትዮጵያ መታሰራቸውን ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቃባይ የኢትዮጵያ “መንግስት ለምን ይሄን እንደሚያደርግ አስተያየት መስጠት አልችልም። ልናገር የምችለው እስር ቤት መሆን የማይገባቸው ባልደረቦቻችን እስር ላይ መሆናቸውን ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ከእነዚህ የተመድ ሰራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ በተለያየ ጊዜ የተለቀቁ ሲሆን፤ በስተመጨረሻ በእስር ቤት የነበሩት ሶስት ብቻ ነበሩ። የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሐመድ ከሳምንት በፊት በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ፤ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የተቋሙ ሰራተኞች እስር አንዱ እንደነበር ዱጃሪች በትላንቱ መግለጫቸው ጠቅሰዋል። ምክትል ዋና ጸሐፊዋ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከሌሎችም ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
ከምክትል ዋና ጸሐፊዋ የኢትዮጵያ ጉብኝት በኋላ፤ በእስር ላይ ከነበሩ ሶስት የተመድ ሰራተኞች ሁለቱ መፈታታቸውን ዱጃሪች ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ አብራርተዋል። ሰራተኞቹ ከእስር የተለቀቁት “ከጥቂት ቀናት በፊት ነው” ያሉት ቃል አቃባዩ፤ “በመፈታታታቸው እጅግ ደስተኞች ነን” ሲሉ አክለዋል።
ዱጃሪች የመጨረሻዎቹ ሶስት ተፈቺዎች በዜግነት ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ለጋዜጠኞች ቢያረጋገጡም፤ ሰራተኞቹ ብሔራቸው ምን እንደሆነ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል አቃባይ “ብሔርን የተመለከተ መረጃ አንሰንድም። ለእኛ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቃባዩ ይህን ቢሉም፤ የተመድ ሰራተኞች በታሰሩበት ጊዜ በወጣ መግለጫ ግን ሁሉም የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው ተገልጾ ነበር። በእስር ላይ ከነበሩ የተመድ ሰራተኞች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ስድስቱ በህዳር ወር ሲለቀቁም የትግራይ ተወላጆች እንደሆኑ መነገሩ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)