በተስፋለም ወልደየስ
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ “ክልሎችን እና የአገር መሪዎችን በማሳነስ ስድብ እና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ” እንዲሁም “አገርን በማሸበር” ወንጀሎች መጠርጠሩን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለፍርድ ቤት አስታወቀ። ጋዜጠኛው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን “ገተት” በሚል ቃል ጠርቷል በሚልም ተወንጅሏል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ይህን ያስታወቀው፤ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ የካቲት 10፤ 2014 ለገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ባቀረበው የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻ ላይ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው በዚህ ባለ ሁለት ገጽ ማመልከቻ ላይ፤ ጋዜጠኛ ታምራት “ተራራ ሚዲያ ግሩፕ በተባለው የግል ሚዲያው በተለያየ ጊዜ እና ቀን” ፈጽሟቸዋል የተባሉ ስምንት ወንጀሎች ተዘርዝረዋል።

በዝርዝሩ ላይ በቀዳሚነት የተቀመጠው ወንጀል ጋዜጠኛው “የእዚህ አገር ህዝብ አካል የሆነው የኦሮሞ ህዝብ አንድነት እንዲፈርስ” አነሳስቷል የሚል ነው። በገላን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መመሪያ አማካኝነት በቀረበው የፍርድ ቤት ማመልከቻ ላይ፤ ታምራት የተጠረጠረበት ሁለተኛ ወንጀልም ከኦሮሚያ ክልል ጋር የተያያዘ መሆኑ ተመላክቷል።
ጋዜጠኛው “የክልሉን መስተዳድር አመራሮችን በስም በመጥቀስ ፕሬዝዳንት ሽመልስ ብሎ ሀሰተኛ ወሬ አሰራጭቷል” በሚል መወንጀሉ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል። ተጠርጣሪው ይህን ያደረገው በኦሮሚያ ክልል ላይ ባለው “ከባድ ጥላቻ” መሆኑ በሰነዱ ላይ ተገልጿል። በዚህ ድርጊቱም “የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት” ተጠርጥሯል ተብሏል።
በፍርድ ቤት ማመልከቻው ላይ ተመሳሳይ የጥላቻ ጉዳይ የተነሳው በስምንተኛ ወንጀልነት በተጠቀሰው ፍሬ ነገር ነው። በዚህ ዝርዝር ላይ ተጠርጣሪው “ይህን ‘ገተት ብሔር ብሔረሰብ ይዘን ኢትዮጵያ የምትባለውን አገር ማሻገር አንችልም በማለት ለአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች ያለውን ከፍተኛ ጥላቻ እና ንቀት በራሱ ሚዲያ ገልጿል” ሲል ሰነዱ አትቷል።
በሰነዱ ላይ የብሔር ብሔረሰቡ ማንነት በስም ባይጠቀስም፤ ማመልከቻው በቀረበበት ዕለት በነበረው የችሎት ውሎ ላይ ግን “ገተት” የሚለውን ቃል ተጠርጣሪው የተጠቀመው፤ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው የፍርድ ቤት ሰነድ ላይ ሰፍሯል። በዚሁ የፍርድ ቤት ውሎን አጠቃልሎ በሚያቀርበው ሰነድ ላይ፤ ጋዜጠኛው “እንደ ቤንሻንጉል ክልል አይነት ገተት የሆኑትን ይዘን የትም መድረስ አንችልም” በሚል መናገሩን እና ይህም በአገር መካከል ጥላቻ እንዲፈጠር በማድረግ ወንጀል የሚያስጠረጥረው መሆኑን ጉዳዩን የያዙት መርማሪ መናገራቸው ተመላክቷል።

“የጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ ወሬ ማሰራጨት” ለብቻው ተነጥሎ በሰነዱ ላይ እንደ አንድ ወንጀል በድጋሚም ተነስቷል። ይህ ወንጀል ራሱን ችሎ የቀረበው፤ ጋዜጠኛው የተጠረጠረባቸው ጉዳዮች በቀረቡበት ዝርዝር ተራ ቁጥር አራት ላይ ነው። ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ አሰራጭቷቸዋል የተባሉ “ወሬዎች”፤ በክልል ደረጃ ሳይወሰኑ ሀገር አቀፍ ጉዳዮችንም የሚመለከቱ እንደሆኑ በፍርድ ቤት ማመልከቻው ላይ ተመላክቷል።
ታምራት “የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ስም በማጥፋት መንግስታቸውን እና አገሪቱን በቻለው መጠን ደረጃ ዝቅ በማድረግ አስቦበት እየሰራ የሚገኝ መሆኑን” ፖሊስ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ማመልከቻ ላይ ተጠቅሷል። እነዚህን ለመለየት ከፍቃድ ሰጪው አካል ለማጣራት ጥያቄ መቅረቡን ፖሊስ በማመልከቻው ጠቁሟል።
ጋዜጠኛውን ባለፈው ሐሙስ ፍርድ ቤት ያቀረቡት መርማሪ በበኩላቸው ተጠርጣሪው “የአገሪቱን [ጠቅላይ ሚኒስትር] ዶክተር አብይን ‘የሚናገረውን ነገር የማያውቅ ሰው፣ ለአገርም ችግር የሆኑ ሰው’ [ናቸው] ” የሚል አገላለጽ መጠቀሙን ለችሎት አስረድተዋል ተብሏል። ጋዜጠኛው “ከዚህ መንግስት ይልቅ የህወሓት መንግስት ይሻላል” ሲል እንደተናገረም መርማሪው ለሐሙሱ ችሎቱ መግለጻቸውን በፍርድ ቤት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።

ታምራት የተጠረጠረበትን ይህን ወንጀል በተመለከተ፤ “ተጠርጣሪው እየተመረመረበት ያለው የወንጀል ድርጊት በልዩ ተልዕኮ በአሸባሪው ህወሓት እና ኦነግ ሸኔ በኢትዮጵያ አገር፣ በዜጎቿ እና በንብረት ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት ባነሰ የሚታይ አይደለም” ሲል ፖሊስ ለፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ ላይ ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቷል።
የህወሓት እና የጦርነቱ ጉዳይ በዚህ ብቻ ሳይበቃ፤ ለፍርድ ቤት በቀረበው ማመልከቻ የወንጀል ዝርዝሮች ላይ በሶስት የተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ ቀርቧል። የፖሊስ ማመልከቻ ሶስተኛ የወንጀል ዝርዝር፤ “አገራችን በአሸባሪው ህወሓት የተከፈተባትን ጦርነት ከአንድ ዓመት በላይ ራሷን እየተከላከለች ባለችበት ጊዜ ውስጥ ተጠርጣሪው የጠላትን ጥቅም የሚያራምዱ ወሬዎች በቪዲዩ (ዩቲዩብ) በመልቀቅ ሲያነሳሳ ቆይቷል” ሲል ጋዜጠኛውን ይወነጅላል።
ስድስተኛው የወንጀል ዝርዝር በበኩሉ “አገራችን ከጥቅምት 23፤ 2014 ወዲህ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለችበት ጊዜ፤ ተጠርጣሪው በተለያየ ጊዜ የአሸባሪውን ህወሓት አላማ ከግብ ለማድረስ ለጉዳዮች ሁኔታ በማመቻቸት፤ የአሸባሪውን አካል የሚያበረታቱ፣ የአገሪቱን ዜጋ የሚያሸብሩ ወሬዎች እየለቀቀ” ቆይቷል ሲል ይከስሳል። በሰባተኛው ዝርዝር ላይ ደግሞ “መንግስት ተገዶ የገባበትን ጦርነት በተመለከተ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ሀሰተኛ ወሬ እና ግራ የሚያጋቡ ነገሮችን ሲያሰራጭ ቆይቷል” ሲል ተጨማሪ ውንጀላ ያቀርባል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ ማጠቃለያ ላይ፤ ተጠርጣሪው “ህዝብን የሚያጋጭ፣ የሚያሸብር እና በሀገር ውስጥ ሁከት ሊያስነሳ የሚችል [መረጃ] በማሰራጨት ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ የሚገኝ በመሆኑ እየተመረመረ እንደሚገኝ” አስታውቋል። “ተጠርጣሪው የተጠረጠረበት ወንጀል ከባድ እና ውስብስብ” መሆኑን የጠቀሰው የክልሉ ፖሊስ፤ “የምርመራ መዝገቡን በሰው ምስክር እና በቴክኒክ ማስረጃ አጣርቶ ስልጣን ላለው አካል እስኪልክ ድረስ” 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል።
ይህ የፖሊስ ማመልከቻ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ታህሳስ 10 የቀረበለት የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ ጉዳዩን የዚያኑ ዕለት ለመመልከት ተሰይሞ ነበር። በዚህ የችሎት ውሎ ያለ ጠበቃ ውክልና የተገኘው ጋዜጠኛ ታምራት፤ “ከዚህ በፊት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆብኝ መዝገብ ተዘግቶልኛል። [የታሰርኩት] በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለሆነ አሁን የጊዜ ቀጠሮ ሊጠየቅብኝም አይገባም። መለቀቅ አለብኝ” ሲል ለፍርድ ቤት አቤት ማለቱ ተመዝግቧል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለዚሁ ፍርድ ቤት ታህሳስ 21 ባስገባው ማመልከቻ፤ በጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ላይ ተከፍቶ የነበረው የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እንዲዘጋ መጠየቁ ይታወሳል። ፖሊስ ኮሚሽኑ መዝገቡ እንዲዘጋ የጠየቀው “ጉዳዩ መታየት ያለበት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሆኑን” በመጥቀስ ነበር።

ፖሊስ “መዝገቡ ስልጣን ላለው አካል እስኪላክ ድረስ በዚህ አዋጅ መሰረት መቆየት ስላለበት፤ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እንዲዘጋልን” በሚል ላቀረበው አቤቱታ፤ የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የሰጠው ምላሽ የይሁንታ ነበር። ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 21፤ 2014 ባስተላለፈው ትዕዛዝ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በደብዳቤ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መዝገቡ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት መመለሱን አስታውቆ ነበር።
ከትላንት በስቲያ በነበረው የችሎት ውሎ ጋዜጠኛ ታምራትን ፍርድ ቤት ይዘው የቀረቡት መርማሪ፤ ከዚህ በፊት በተጠርጣሪው ላይ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቃቸውን እና መዝገቡም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መዘጋቱን አምነዋል። ሆኖም “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነሳ ስለሆነ ቀጥሎ እንዲታይልን” ሲሉ መርማሪው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን በችሎት ውሎ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።
የግራ ቀኙን አስተያየት ያደመጡት ዳኛ፤ “ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን ጉዳይ በተመለከተ፤ ከዚህ በፊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢዘጋም፤ በአሁኑ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለተነሳ በመደበኛ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮ ማየት የሚችል ስለሆነ፤ አመልካች ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን ጉዳይ በሰባት ቀን ጊዜ ውስጥ እንዲያጣራ” ማለታቸው በፍርድ ቤቱ ሰነድ ላይ ተቀምጧል።

ለስድስት ወራት ተደንግጎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከሶስት ወራት ቆይታ በኋላ በፓርላማ የተነሳው ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 8፤ 2014 ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ቆይታ እንዲያጥር ያደረገው ፓርላማው፤ የፍትህ አካላት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የጀመሯቸውን ጉዳዮች በመደበኛው የፍትህ አሰጣጥ ስርዓት እንዲያጠናቅቁ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት የቀረበው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ የምርመራ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀበት፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከአንድ ወር ከሃያ ቀን በፊት “በምርመራ አጣርቼ ደርሼባቸዋለሁ” ያላቸውን ስምንት ጉዳዮች በድጋሚ በማንሳት ነው። የጋዜጠኛውን ጉዳይ ከዚህ ቀደም ሲመለከት የቆየው የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ በፖሊስ የተጠየቀውን የ14 የምርመራ ቀናት በመቀነስ በድጋሚ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል።
ፍርድ ቤቱ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በነበረው የችሎት ውሎው፤ “ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን ጉዳይ በሰባት ቀናት ውስጥ አጣርቶ ውጤቱን እንዲያቀርብ” ለፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቷል። በዚህም መሰረት ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ በመጪው ሐሙስ የካቲት 17 በተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ይቀርባል።

“ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታምራት ነገራ፤ በፖሊስ ከመኖሪያ ቤቱ ከተወሰደ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለው ታህሳስ 1፤ 2014 ነው። ላለፉት 71 ቀናት በእስር ላይ የቆየው ጋዜጠኛ ታምራት፤ “እንደ አዲስ የተጀመረበት ምርመራ ተቋርጦ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መለቀቅ አለበት” ሲል ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) ትላንት አርብ የካቲት 11 ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።
የመብት ተሟጋቹ በዚሁ መግለጫው እንደ ታምራት ሁሉ በእስር ላይ የሚገኙት፤ የአሶሴትድ ፕሬስ ፍሪላንስ ዘጋቢ አሚር አማን እና የካሜራ ባለሙያው ቶማስ እንግዳ ላይ መደበኛ ክስ ለመመስረት መታቀዱን ኮንኗል። በሲፒጄ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን ጉዳይ የሚከታተሉት ሙቱኪ ሙሞ፤ የጋዜጠኞቹን አግባብ ያልሆነ እስር የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላለፉት ለሶስት ወራት ለመከላከል ሲሞክሩ የቆዩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጥቀስ እንደሆነ ተናግረዋል።
“የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን ተከትሎ በእነዚህ ጋዜጠኞች ላይ አዲስ የፍርድ ቤት ሂደቶችን እና ምርመራዎች መጀመሩ፤ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋዜጠኞቹን በእስር ቤት ለማቆየት የሚያደርጉት ግልጽ እና የሚያበሳጭ ሴራ ነው” ሲሉ የሲፒጄዋ ወኪል ተችተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫም የጋዜጠኛ ታምራት ነገራን ጉዳይ በመጥቀስ ተመሳሳይ ትችት ሰንዝሯል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ በርካቶች መለቀቃቸውን በበጎ ጎኑ እንደሚያዩት ገልጸው፤ ሆኖም በ48 ሰዓት ውስጥ የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው እስራቸው እንዲራዘም የተደረጉ ሰዎች ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው በኮሚሽኑ መግለጫ አስታውቀዋል።
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች ላይ የመንግስት ባለስልጣናት አሳማኝ ክስ ቢኖራቸው ኖሮ ይህንኑ አስቀድመው ለፍርድ ቤት ያቀርቡ እንደነበር የሚከራከሩት ዶ/ር ዳንኤል፤ እየሆነ ያለው ግን እስሮችን ለማራዘም የጊዜ ቀጠሮ ስነ ስርዓቶችን አላግባብ የመጠቀም አካሄድ እንደሆነ አብራርተዋል። የጋዜጠኛ ታምራትን ጉዳይ በማሳያነት የጠቀሱት ኮሚሽነሩ፤ እርሱን በጊዜ ቀጠሮ ለማቆየት “ህጋዊ ምክንያት የለም” ብለዋል።

“ተፈጸመ የተባለ ማንኛውም የጋዜጠኝነት ጥፋት፤ ለተራዘመ እስር ይቅር እና ከክስ በፊት ለሚደረግ ማንኛውም እስር አይዳርግም” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ የጋዜጠኛ ታምራት እስር “ህጋዊ መሰረት አለው” ቢባል እንኳ የጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀበት አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ አስረድተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ 48 ሰዓት ሊሞላው አንድ ሰዓት ሲቀረው በጋዜጠኛው ላይ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቁ፤ “ስልጣንን አላግባብ መጠቀም እና እርቃኑን የቀረ ኢ-ፍትሃዊነት የሚያመላክት ነው” ሲሉ ኮሚሽነሩ ተችተዋል።
የጋዜጠኛ ታምራት ጉዳይ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ በወጣው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር መግለጫ ላይም ተነስቷል። ማህበሩ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው “ተደጋጋሚ እስር እና እንግልት” እንዲቆም በጠየቀበት መግለጫው፤ “ታምራት ነገራ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እስካሁን በእስር ላይ መቆየቱ እጅግ አሳዛኝ እና ተገቢነት የሌለው ተግባር መሆኑን ማህበራችን ያምናል” ብሎ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)