በሃሚድ አወል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን በኮሚሽነርነት የሚመሩ የ11 ኮሚሽነሮችን ሹመት ሊያጸድቅ ነው። ምክር ቤቱ ነገ ሰኞ የካቲት 14 በሚያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የኮሚሽነሮችን ሹመት ማጽደቅ በዋና አጀንዳነት መያዙን ሶስት የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
በነገው የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ፤ የዕጩ ኮሚሽነሮችን ሹመት ለማጽደቅ የቀረበ አራት ገጽ የውሳኔ ሃሳብ በንባብ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ የውሳኔ ሃሳብ፤ ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኮሚሽነርነት የሚቀርቡ ዕጩዎችን ጥቆማ ከመቀበል እስከ ሹመት የታለፈበትን ሂደት ዘርዝሯል።
ከሁለት ወር ገደማ በፊት ታህሳስ 20፤ 2014 የጸደቀው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ የምክክር ኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንደሚኖሩት ይደነግጋል። በአዋጁ መሰረት ለኮሚሽነርነት የሚቀርቡ ዕጩዎችን የመቀበል ኃላፊነት የተሰጠው ለተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ነው።
ጽህፈት ቤቱ ሶስት አባላት ያሉት የዕጩ ኮሚሽነሮች ጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴ በማቋቋም፤ ከታህሳስ 26፤ 2014 ጀምሮ የተጠቆሙ ግለሰቦችን ዝርዝር መረጃ ሲቀበል ቆይቷል። ለሶስት ሳምንታት በዘለቀው የጥቆማ ማቅረቢያ ጊዜ ውስጥ፤ 632 ግለሰቦች ለዕጩ ኮሚሽነርነት ተጠቁመዋል። ከህዝብ፣ ከፖለቲካ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበራት የቀረቡትን እነዚህን ተጠቋሚዎች፤ “በሶስት ምድብ” በመክፈል የመለየት ስራ መከናወኑ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተመልክቷል።
የጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴው ግለሰቦቹን ለመለየት የተጠቀመው፤ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ የተቀመጡትን ዘጠኝ መስፈርቶች መሆኑም ተገልጿል። ዕጩዎች ሊያሟሏቸው ከሚገቡ መስፈርቶች መካከል፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው መሆኑ፤ ሁሉንም ሃይማኖቶች፣ የተለያዩ ብሔሮችን እና ሕዝቦችን በእኩል ዓይን የሚያዩ መሆናቸው እንዲሁም የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆናቸው ይጠቀሳሉ።
በእነዚህ መስፈርቶች ተመዝነው በመጀመሪያ ምድብ የተካተቱት 42 ግለሰቦች፤ ኮሚቴው “ለእጩነት ቢቀርቡ ‘ብቁ ናቸው’ ብሎ የለያቸው” እንደሆኑ በውሳኔ ሀሳቡ ሰፍሯል። በሁለተኛው ምድብ የተካተቱ ግለሰቦች ብዛት 75 ሲሆን ኮሚቴው “በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚደረጉ የምክክር መድረኮች እንደ አወያይ ሊያገለግሉ ይችላሉ” በሚል የመረጣቸው ናቸው።
የጥቆማ ተቀባይ ኮሚቴው፤ “የምልመላ ሂደቱን ያላሟሉ” ያላቸውን 515 ተጠቋሚዎችን ለብቻ በሶስተኛ ምድብ ለይቶ ማስቀመጡ በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ተብራርቷል። በእነዚህ ሶስት ምድቦች ውስጥ ከተካተቱ ተጠቋሚ ግለሰቦች ውስጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማንነታቸውን ይፋ ያደረገው፤ በመጀመሪያው ምድብ የተካተቱትን 42 ዕጩዎችን ነው።
ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ይፋ ከተደረጉት ከእነዚህ ዕጩዎች መካከል አስራ ሶስቱ ፕሮፌሰሮች ሲሆኑ አስራ ሁለቱ ደግሞ የዶክትሬት ማዕረግ ያላቸው ናቸው። በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ አራት የቀድሞ አምባሳደሮችም ተካትተዋል።
የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ “አፈ ጉባኤው የሚያዘጋጇቸው የዕጩዎች ዝርዝር የጾታ እና ሌሎች የብዝሃነት መገለጫዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል” ቢልም፤ በዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ሴቶች አራት ብቻ መሆናቸው አነጋግሯል። የተወካዮች ምክር ቤት አርባ ሁለቱን ዕጩ ኮሚሽነሮችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት ላይ፤ የጾታ እና የዕድሜ ውክልና እና ስብጥር ጉዳይ ተነስቶ ነበር።
ከሲቪክ ማህበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በተደረገው በዚሁ ውይይት፤ የዕጩዎቹ ዝርዝር “ልሂቅ ተኮር ነው” የሚል ትችት ተሰንዝሮበታል። ለፓርላማ አባላት ሰኞ በንባብ ይቀርባል ተብሎ በሚጠበቀው የውሳኔ ሃሳብ ላይ፤ “የህዝብ አስተያቶችን ተከትሎ የብዝሃነትን፣ ጾታን እና ዕድሜን መሰረት ያደረገ ማስተካከያ” መደረጉ ተገልጿል።
“አንዳንድ ዕጩዎች ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጻቸው እና አንዳንዶቹ በአዋጁ መሰረት የተደነገጉ መስፈርቶችን የማያሟሉ በመሆናቸው በሁለተኛ ደረጃ ተይዘው በነበሩ ዕጩዎች እንዲተኩ ተደርጓል” ሲል የውሳኔ ሃሳቡ የተደረገውን “ማስተካከያ” አብራርቷል። የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ፤ ከ42ቱ ዕጩ ኮሚሽነሮች መካከል በአዋጁ የተቀመጡ መስፈርቶችን የማያሟሉ ዕጩዎች ተካትተውበታል ማለቱ ይታወሳል።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ “የሁለት ሀገር ዜግነትን የያዙ፣ የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ያላቸው እና በወንጀል ተከስሰው የሚያውቁ ተካትተውበታል” ሲሉ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። የዕጩ ኮሚሽነሮች አመራረጥ አካሄዱ “አሳታፊ አልነበረም” ሲሉ የሚተቹት ዶ/ር ራሄል፤ የአገራዊ ምክክር ሂደቱ ከባለድርሻ አካላት የተሰጡ “ግብዓቶችን” አለማካተቱንም በማሳያነት አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢዋ የአገራዊ ምክክር ሂደቱ “አሳታፊ አልነበረም” ብለው ቢተቹትም፤ ለፓርላማ አባላት በሚቀርበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ግን ሂደቱ “አሳታፊ፣ ግልጽ፣ ተአማኒነት ያለው እና ገለልተኝነትን ያረጋገጠ እንዲሆን ተደርጎ የተከናወነ ነው” በሚል ተገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)