የተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን ሹመት አጸደቀ

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ የካቲት 14 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽንን 11 ኮሚሽነሮች ሹመት አጸደቀ። ምክር ቤቱ የኮሚሽነሮችን ሹመት ያጸደቀው በአብላጫ ድምጽ ነው። 

“ሁሉን አቀፍ እና አካታች ምክክር ያካሄዳል” ለተባለው ኮሚሽን የሚያገለግሉት ኮሚሽነሮች ሹመት ከፓርላማ አባላት ምንም ተቃውሞ አልገጠመውም። በዛሬው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 335 የፓርላማ አባላት አምስቱ ድምጽ ከመስጠት ሲታቀቡ ቀሪዎቹ ሹመቱን ደግፈዋል።  

ሹመቱን ከመጽደቁ በፊት፤ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ለምክር ቤቱ አባላት የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በንባብ አሰምተዋል። በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ኮሚሽነሮችን የመሰየም ስልጣን የተሰጣቸው አፈ ጉባኤው፤ ዋና ኮሚሽነር፣ ምክትል ኮሚሽነር እና ኮሚሽነር ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ ዕጩዎችንም ለፓርላማ አባላቱ አቅርበዋል። 

አፈ ጉባኤው ካቀረቧቸው 11 ኮሚሽነሮች መካከል ፕ/ር መስፍን አርአያ ኮሚሽኑን በሰብሳቢነት እንዲመሩ መርጠዋቸዋል። ፕ/ር መስፍን አርአያ ከዩኒቨርስቲ መምህርትነት ጀምሮ እስከ ሆስፒታል ዳይሬክተርነት 50 ዓመታት ገደማ የስራ ልምድ አላቸው። የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስቱ ፕሮፌሰር፤ ከሶስት ዓመታት በፊት በተቋቋመው የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባል ናቸው። 

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በምክትል ሰብሳቢነት እንዲመሩ የተሾሙት ወ/ሮ ሂሩት ገብረስላሴ ናቸው። የፈረንሳዩ ሶርቦርን ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሩቅ የሆኑት ወይዘሮ ሂሩት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል። አርባ ዓመታት ገደማ በስራ ላይ የቆዩት የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ፤ አብዛኛውን የስራ ዘመናቸውን ያሳለፉት በተባበሩት መንግስታት ስር ባሉ ድርጅቶች እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በመስራት ነው። 

የተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባው ሹመታቸውን ካጸደቀላቸው 11 ኮሚሽነሮች መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው። ምክትል ሰብሳቢዋን ጨምሮ በኮሚሽነርነት የተመረጡት ሴቶች የህግ ትምህርት ምሩቃን ናቸው። ዶ/ር አይሮሪት መሐመድ ከኔዘርላንዱ አምስተርዳም ዩኒቨርስቲ በህግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን፤ ወ/ሮ ብሌን ገብረመድህን ደግሞ በዓለም አቀፍ ህግ እና በሰብዓዊ መብት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከስዊዘርላንድ ይዘዋል።  

ዶ/ር አይሮሪት ረዥም የስራ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በዩኒቨርሲቲ መምህርነት ነው። አዲሷ ተሿሚ በአፋር ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለሶስት ዓመታት በዳኝነት ያገለገሉ ሲሆን፤ በህግ አማካሪነትም ለሁለት ዓመታት ሰርተዋል። ከታህሳስ 2011 ጀምሮ ላለፉት ሶስት ዓመታት በኦማን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነበሩ።

አስራ አንድ ዓመት የስራ ልምድ ያላቸው ወ/ሮ ብሌን፤ የኮሚሽነርት ሹመት እስካገኙበት ዕለት ድረስ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። ኮሚሽነሯ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት ያህል አስተምረዋል። 

ከአስራ አንዱ ኮሚሽነሮች ውስጥ በከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከፍተኛ ስም ያላቸው መሐሙድ ድሪር ተካትተዋል። አምባሳደር መሐሙድ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የተለያዩ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን በሚኒስትርነት መርተዋል። 

መሐሙድ በዚምባቡዌ እና በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። አምባሳደሩ በሱዳን የሽግግር መንግስት ምስረታ ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው አበይት ሚና ተጫውተዋል።

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በአባልነት ከተቀላቀሉ ተሿሚ ኮሚሽነሮች መካከል በደርግ ዘመነ መንግስት የግብርና እንዲሁም መሬት ይዞታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ዘገየ አስፋው ይገኙበታል። አቶ ዘገየ እንደ ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕ/ር መስፍን ሁሉ፤ እስከ አዲሱ የኮሚሽነርነት ሹመታቸው ድረስ በአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በአባልነት ቆይተዋል።   

ዛሬ ሹመታቸው በፓርላማ ከጸደቀላቸው 11 ኮሚሽነሮች ውስጥ ሶስቱ፤ የተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ይፋ ባደረገው የ42 ዕጩ ኮሚሽነሮች ስም ዝርዝር ውስጥ አልተካተቱም ነበር። በዚህ ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱት ኮሚሽነሮች ዶ/ር አምባዬ ኦጋቶ፣ ወ/ሮ ብሌን ገብረመድህን እና አቶ ሙሉጌታ አጎ ናቸው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የውሳኔ ሃሳቡን ለፓርላማ አባላት በንባብ ባሰሙበት ወቅት “የህዝብ አስተያቶችን ተከትሎ የብዝሃነትን፣ ጾታን እና ዕድሜን መሰረት ያደረገ ማስተካከያ” መደረጉን ተናግረዋል። “አንዳንድ ዕጩዎች ፍላጎት እንደሌላቸው በመግለጻቸው እና አንዳንዶቹ በአዋጁ መሰረት የተደነገጉ መስፈርቶችን የማያሟሉ በመሆናቸው በሁለተኛ ደረጃ ተይዘው በነበሩ ዕጩዎች እንዲተኩ ተደርጓል” ሲሉ “ማስተካከያውን” አብራርተዋል። 

የተወካዮች ምክር ቤት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተጠቆሙ 632 ግለሰቦች ውስጥ 75 ያህሉን በሁለተኛ ደረጃ ተመራጭነት ይዟቸው ነበር። የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ሲቀበል የቆየው የምክር ቤቱ ኮሚቴ እነዚህ ግለሰቦች በአንድ ምድብ አድርጎ ያስቀመጠው፤ “በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚደረጉ የምክክር መድረኮች እንደ አወያይ ሊያገለግሉ ይችላሉ” በሚል እንደነበር በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ተብራርቷል።  

በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ቀደም ሲል ማንነታቸው ይፋ ከተደረጉ ውጭ አዳዲስ ግለሰቦች መካተታቸው በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ጥያቄ ባያስነሳም፤ አጠቃላይ የአመራረጥ ሂደቱ ግን ጉዳዩ ይመለከታቸዋል በሚባሉ ባለድርሻ አካላት ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል። ከትችቶቹ መካከል አንደኛው ዕጩዎች የሚመረጡበት መስፈርት “ግልጽ አይደለም” የሚል ነው።

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች መግለጫ አውጥተዋል። እነዚህ አካላት አርባ ሁለቱ ዕጩ ኮሚሽነሮች “የተመረጡበት መስፈርት ግልጽ ይሁን” የሚል ጥያቄ ቢያነሱም፤ ከተወካዮች ምክር ቤት ይፋዊ ምላሽ ሳይሰጥበት ለዛሬው የኮሚሽነሮች ሹመት ቀን ተደርሷል። 

በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ፤ የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከመቀበል እስከ ሹመት የታለፈበት ሂደት የተብራራበትን የውሳኔ ሃሳብ በንባብ ያሰሙት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ከባለ ድርሻ አካላት ስለ አመራረጥ ሂደቱ ይቀርብ ስለነበረው ቅሬታ ሳይጠቅሱት አልፈዋል። ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም እንዲሁ አልገለጹም።  

በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት የኮሚሽኑን ኮሚሽነሮች የመሰየም ኃላፊነት የተሰጠው ለተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ለአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ነው። የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤቱ፤ የዕጩ ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከህዝብ፣ ፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማህበራት ከተቀበለ በኋላ፤ በአዋጁ ላይ በተቀመጡ ዘጠኝ መስፈርቶች መሰረት ዕጩ ኮሚሽነሮችን እንደሚመርጥ ተደንጓል። 

ለኮሚሽርነት ከሚያበቁ መስፈርቶች መካከል፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው መሆን፣ የማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆን፣ በከባድ ወንጀል ተከስሰው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያልተላለፈባቸው መሆን እና ሙሉ ጊዜያቸውን ለኮሚሽኑ ስራ ለማዋል ፍቃደኛ መሆን ይገኙባቸዋል። እነዚህን የመምረጫ መስፈርቶች ማሟላታቸው በአፈ ጉባኤው ከተመሰከረላቸው እና ሹመታቸው በፓርላማ ከጸደቀላቸው 11 ኮሚሽነሮች መካከል፤ ዘጠኙ በአካል ተገኝተው ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።

ዛሬ ከተሾሙት 11 ኮሚሽነሮች መካከል በፓርላማ ያልተገኙት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ እና ዶ/ር ተገኘወርቅ ጌጡ ናቸው።  ዶ/ር ዮናስ የሰላምና ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩትን በዋና ዳይሬክተርነት እየመሩ ያሉ ናቸው። ዶ/ር ተገኘወርቅ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)