የአባይ ግድብ በሚገነባበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ያለው የጸጥታ መጓደል፤ የግንባታውን ሂደት ተፈታትኖት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሁለት ሳምንታት እንኳን በአካባቢው ጸጥታ የሚያስከበሩ ከአምስት በላይ ወታደሮች መገደላቸውን ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት የአባይ ግድብ የግንባታ ሂደት ገጥመውት ስለነበሩ ተግዳሮቶች ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 15፤ 2014 ለተወካዮች ምክር ቤት ባብራሩበት ገለጻቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ችግሮችን የሚፈጥሩ ኃይሎችን ማንነት በንግግራቸው ባይገልጹም፤ ግድቡ በሚገነባበት አካባቢ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ግን ዘርዝረዋል።
“ፋብሪካ ላይ መጥተው ሰው ያፍናሉ፤ ሲሚንቶ ጭኖ የሚሄድ ሾፌር ይገድላሉ። ሲሚንቶ ጭኖ የሚሄድ ሹፌር በፓትሮል ስናጅብ ደግሞ ፈንጂ ይቀብራሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለግድቡ ግንባታ የሚያስፈልገውን ሲሚንቶ ለማድረስ እንኳን “ፈተና” እንደነበር አስረድተዋል።
በህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚሳተፉ የውጪ ዜጎች ለቅቀው ለመውጣት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው ጠቅሰዋል። “ህዳሴ ያሉ የውጭ አገር ሰዎች እየከፈልናቸው አንሰራም፤ ካልወጣን አሉ። ከውጪ የምናስገባው በርካታ ነገር በየቦታው ተያዘ። ከጅቡቲ እንኳ የምናመጣው ትላልቅ ግብዓት የሚሆኑ እቃዎች ተስተጓጎለ” ሲሉ የነበረውን ችግር አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)