በጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ላይ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

ላለፉት 76 ቀናት በእስር ላይ በሚገኘው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ ላይ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ። የታምራትን ጉዳይ የሚመለከተው የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የጊዜ ቀጠሮውን የፈቀደው፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የተጠርጣሪውን “ስልክ፣ ሚሞሪ ካርድ እና ኮምፒዩተሮች ለመመርመር ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል” በማለቱ መሆኑን የጋዜጠኛው ጠበቃ አቶ ገመቹ ጉተማ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት በተፈቀዱለት ሰባት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማዳመጥ ነበር።  ፖሊስ በተፈቀዱለት ጊዜያት “ተጠርጣሪው የተጠረጠረበትን ጉዳይ አጣርቶ ውጤቱን እንዲያቀርብ” በፍርድ ቤት ቢታዘዝም፤ በዛሬው የችሎት ውሎ ግን “ምርመራዬን አልጨረስኩም” ማለቱን ጠበቃ ገመቹ ገልጸዋል። 

የኦሮሚያ ፖሊስ “ሞባይል፣ ሚሞሪ እና ኮምፒዩተሮች እየመረመርን ነው። ይኼንን የሚመረምረው አካል ደግሞ የስራ ብዛት አለበት። ስለዚህ ይኼንን ለማድረግ አሁንም ጊዜ ያስፈልገናል” የሚል ምክንያት በማቅረብ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ መጠየቁን የጋዜጠኛው ጠበቃ አስረድተዋል። ይህንን ተከትሎም ጠበቃው፤ ፖሊስ “ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድለት አይገባም” በሚል ሶስት መከራከሪያቸውን ለፍርድ ቤቱ አሰምተዋል።

የጋዜጠኛው ጠበቃ በመጀመሪያ ያቀረቡት መከራከሪያ፤ ጋዜጠኛው የተጠረጠረባቸው ወንጀሎች ተፈጸሙ ከተባሉበት መንገድ ጋር ይያዛል። ታምራት ነገራ የተጠረጠረባቸው ወንጀሎች በሚዲያ አማካኝነት ተፈጸሙ የተባሉ ወንጀሎች መሆናቸውን የጠቀሱት ጠበቃው፤ “በዚህ ጉዳይ ጊዜ ቀጠሮ መስጠት አይቻልም። ህጉም አይፈቅድም። ክልከላ አድርጓል” ብለው መከራከራቸውን አስረድተዋል። 

እንደ አቶ ገመቹ ገለጻ፤ በሚዲያ አማካኝነት ወንጀል ፈጸመ የተባለን ሰው፤ ለተጨማሪ ምርመራ ማሰር ሳይስፈልግ በቀጥታ ወደ ክስ እንደሚገባ በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ ተደንግጓል። አዋጁ “አቃቤ ህግ መረጃዎችን አጠናቅሮ፤ ቀጥታ በፍርድ ቤት ክስ እንዲመሰረት ነው የሚደነግገው” ሲሉ መከራከሪያቸውን ለገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ማቅረባቸውን ገልጸዋል። 

ሁለተኛው የጠበቃው መከራከሪያ ታምራት ነገራ የተጠረጠበት ወንጀልን የሚመለከት ነው። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የዛሬ ሳምንት ሐሙስ፤ ባቀረበው ባለ ሁለት ገጽ የምርመራ ጊዜ ቀጠሮ ማመልከቻ ጋዜጠኛ ታምራት ነገራን በስምንት ወንጀሎች እንደጠረጠረው አስታውቆ ነበር። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው ማመልከቻ፤ ወንጀሎቹ ጋዜጠኛው “ተራራ በተባለው የግል ሚዲያው በተለያየ ጊዜ እና ቀን” ፈጽሟቸዋል የተባሉ ናቸው።  

ጋዜጠኛ ታምራት ከተጠረጠረባቸው ወንጀሎች መካከል አንዱ የሆነው “የሽብር ወንጀል” በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታይ መሆኑን ለችሎቱ የተናገሩት ጠበቃው፤ የገላን ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት “በዚህ ጉዳይ የጊዜ ቀጠሮ የመሰጠት ስልጣን የለውም” ብለው መሟገታቸውን ተናግረዋል። አቶ ገመቹ “የሽብር ወንጀሎች የሚመረመሩት በፌደራል ፖሊስ ስለሆነ የኦሮሚያ ፖሊስ የመመርመር ስልጣን የለውም የሚል መከራከሪያ አቅርበናል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ጠበቃው በሶስተኛ መከራከሪያነት ያነሱት ጉዳይ፤ ጋዜጠኛው በእስር ላይ የቆየበት ጊዜ ምርመራ ለማካሄድ በቂ መሆኑን ነው። ጋዜጠኛ ታምራት ከታሰረ 77 ቀናት እንደሆነው ለችሎቱ የገለጹት ጠበቃው፤ “ምርመራ ለማድረግ፤ ክስም ከፍቶ የፍርድ ቤትን ውሳኔ ለማግኘትም በቂ የሚባል ጊዜ ስለሆነ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት የለበትም” ሲሉ የፖሊስን ጥያቄ ተቃውመዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የተጠርጣሪው ጠበቃ ላቀረቧቸው መከራከሪያዎች ምላሽ እንዲሰጥ በፍርድ ቤቱ ዕድል ተሰጥቶት እንደነበር አቶ ገመቹ ገልጸዋል። ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፤ “በሚዲያ ብቻ የተፈጸመውን [ወንጀል] አይደለም እየመረመርን ያለነው። ከሚዲያ ውጭም የፈጸማቸውን ተግባሮችም ጨምሮ ነው” ማለቱን ጠበቃው ተናግረዋል።

አቶ ገመቹ በዚህ የፖሊስ መከራከሪያ ላይ የመልስ መልስ በሰጡበት ወቅት፤ ፖሊስ ደንበኛቸው ፈጽሟቸውዋል ያላቸውን ተግባራት የጠቀሰው “በሚዲያ ለተፈጸሙ ወንጀሎች የጊዜ ቀጠሮ እንደማይሰጥ” ስለሚታወቅ ነው ብለዋል። ፖሊስ ደንበኛው ከሚዲያ ውጭ ፈጽሟቸዋል ላላቸው ተግባራት “ምንም ማስረጃ የለውም” ሲሉ ለችሎቱ መናገራቸውንም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

“ፖሊስ [ከዚህ በፊት] ለፍርድ ቤቱ ‘ከሚዲያ ውጭ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እየመረመርኩ ነው’ የሚል ጥያቄ አላቀረበም። የወንጀል የምርመራ መዝገቡም ቢታይ ከሚዲያ ውጭ የተፈጸመ ጉዳይ አለ ተብሎ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የሚያሳይ ምንም ነገር የለም” ሲሉም ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የገላን ወረዳ ፍርድ ቤት፤ ጠበቃው ያቀረቡትን መከራከሪያ ውድቅ በማድረግ ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። ፍርድ ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “TPLF [ህወሓት] እና ኦነግ ሸኔን በመደገፍ፣ በማነሳሳት የሚሉ ወንጀሎች ስላሉ ይኼ ደግሞ የምርመራ ጊዜ ስለሚያስፈልገው ነው” በሚል ምክንያት እንደሆነ አቶ ገመቹ አብራርተዋል። 

ፍርድ ቤቱ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በተፈቀደለት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜያት ያከናወናቸውን ተግባራት ለመጠበቅ ለመጋቢት 1፤ 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የዛሬውን ችሎት አጠናቅቋል። “ተራራ ኔትወርክ” የተባለው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ የሆነው ታምራት ከቤቱ ተወስዶ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ታህሳስ 1፤ 2014 ነበር። ጋዜጠኛው አሁን በእስር ላይ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ስር ባለው ገላን ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)