አሜሪካ በኢትዮጵያ በሚገኘው ኤምባሲዋ እንዲያገለግሉ የመደበቻቸው ዲፕሎማት ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ ዛሬ አርብ የካቲት 18 አዲስ አበባ መግባታቸውን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ። ትሬሲ ጃኮብሰን በዚህ ሳምንት በይፋ የተሰናበቱትን የአሜሪካ አምባሳደር ጊታ ፓሲን በ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ በጊዜያዊነት የሚተኩ ናቸው።
ትሬሲ በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መሾማቸው ይፋ እስከሆነበት ዕለት ድረስ፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። ዲፕሎማቷ ከዚህ ቀደም በኮሶቮ፣ ታጃኪስታን እና ቱርክሜንስታን የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ሰርተዋል።
በኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት በአምባሳደርነት ያገለገሉት ጊታ ፓሲ፤ ኃላፊነታቸውን የለቀቁት “ጡረታ ለመውጣት በማቀዳቸው” መሆኑ ባለፈው ጥር ወር ተገልጾ ነበር። አምባሳደር ጊታ ከዓመት በፊት የሹመት ደብዳቤያቸውን ከተቀበሏቸው ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ባለፈው ሰኞ የካቲት 14 ተገናኝተው በይፋ ተሰናብተዋል።
በአሜሪካ ኤምባሲ ከሙሉ አምባሳደርነት ቀጥሎ ሁለተኛ ከፍተኛ የስልጣን ቦታ የሆነውን የ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ የያዙት ትሬሲ ጃኮብሰን ወደ አዲስ አበባ የመጡት፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ የሻከረው የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ሀገራት ግንኙነት የመሻሻል አዝማሚያ ባሳየበት ወቅት ነው። የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተገኙበት የፓርላማ ስብሰባ ላይም ተነስቶ ነበር።
ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 15 በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሜሪካንን “ወዳጅ አገር” ሲሉ ጠርተዋታል። “አሜሪካ ጥቅም አላቸው እኛም ጥቅም አለን፤ እየተመካከርን እየተነጋገርን ለጋራ ጥቅማችን በጋራ እንሰራለን። መፍትሔው እሱ ነን ሲሉ ሁለቱ ሀገራት በትብብር እንደሚሰሩ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)