ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በድርቅ ምክንያት ሕጻናት እና አረጋውያን እየሞቱ ነው አሉ

በተስፋለም ወልደየስ

በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ድርቅ ያስከተለው ረሃብ የሕጻናት እና አረጋውያን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። በእነዚህ አካባቢዎች ላሉ ወገኖች ክረምት እስኪደርስላቸው የሚጠበቅ ከሆነ፤ ብዙ ሰዎች ሊሞቱ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያስታወቁት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ አርብ የካቲት 18 ምሽት ባስተላለፉት መልዕክት ነው። በኢትዮጵያ በተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ የዳሰሰው የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት፤ በሶማሌ ክልል እና ቦረና አካባቢ ችግሩ አሁን የደረሰበት ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል።

በሁለቱ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አርብቶ አደሮች “በአሁኑ ሰዓት በድርቅ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ” የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በእነዚህ አካባቢ ያሉ ወገኖች የሚያረቧቸው ከብቶቻቸው “በመኖ እና ውሃ እጦት እየረገፉ ነው” ሲሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሶማሌ ክልል እና ቦረና አካባቢ ያሉ አርብቶ አደሮች “በመኖ እና ውሃ እጦት እየረገፉ ነው” ሲሉ በመልዕክታቸው አስፍረዋል | ፎቶ፦ ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ማክሰኞ በፓርላማ በነበራቸው የጥያቄ እና መልስ ወቅት በድርቅ ምክንያት “ሰው አልሞተብንም” ቢሉም፤ ከሁለት ቀናት ቆይታ በኋላ ዛሬ ባስተላለፉት መልዕክት ግን በድርቅ ምክንያት ህጻናት እና አረጋውያን መሞት መጀመራቸውን አስታውቀዋል። “ድርቁ ያስከተለው ረሃብ የሕጻናቱንና እና የአረጋውያኑን ሕይወት እያሳጣ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖች ሁሉም አቅሙ የፈቀደውን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። 

በድርቅ ለተጎዱት አካባቢዎች የሚደረገው እርዳታ የሚዘገይ ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት በሰው ህይወት ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት በላቀ የበርካቶች ሞት ሊከተል እንደሚችል በጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ላይ ተመላክቷል። ለሶማሌ እና ቦረና አርብቶ አደሮች “ክረምቱ እስኪደርስላቸው እንጠብቅ ከተባለ ብዙ ወገኖቻችንን እናጣለን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አስጠንቅቀዋል።

በኢትዮጵያ በሶስት ክልሎች የተከሰተው ድርቅ ጉዳይ ባለፈው ማክሰኞ በነበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይም ተነስቶ ነበር። ከሶማሌ ክልል የኤረር አካባቢን የወከሉት ፋራህ መሐመድ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ እርሳቸው በተመረጡበት ክልል “ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ” ድርቅ መከሰቱን ተናግረዋል።

ከሶማሌ ክልል የኤረር አካባቢን የወከሉት ፋራህ መሐመድ የተባሉ የፓርላማ አባል፤ እርሳቸው በተመረጡበት ክልል ካሉት 93 ወረዳዎች በሰማንያ ስድስቱ ድርቅ መከሰቱን አብራርተዋል

በሶማሌ ክልል ካሉት 11 ዞኖች አስሩ በድርቅ መጠቃታቸውን የገለጹት የፓርላማ ተወካዩ፤ ክልሉ ካሉት 93 ወረዳዎች በሰማንያ ስድስቱ ድርቅ መከሰቱን አብራርተዋል። በክልሉ የተከሰተው ድርቅ “ባለፉት 40 ዓመታት ባልታየ ሁኔታ የከፋ ነው” ሲሉ የችግሩን ጥልቀት አጽንኦት ሰጥተዋል።  

“[ድርቁ] አሁን በአደገኛ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቶ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የዕለት ጉርስ ጠባቂ ሲሆኑ፤ ከ800 ሺህ በላይ እንስሳት ሞተዋል። ከ1,100 በላይ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ከ150 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት እንዳልቻሉ በክልሉ ያለው መረጃ ይጠቁማል” ሲሉም አቶ ፋራህ ችግሩን ያስከተለውን ጉዳት አስረድተዋል። 

የፓርላማ አባሉ ከዚህ ገለጻቸው ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባቀረቡት ጥያቄ፤ የተከሰተው ድርቅ ወደ ረሃብ ተሸጋግሮ የሰው ህይወት እንዳይቀጥፍ እና በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙት እንስሳት እንዳይሞቱ ለማድረግ መንግስት ምን አይነት ስራዎች እየሰራ እንደሆነ ማብራሪያ ጠይቀዋል። “አርብቶ አደሩ ህዝባችን ለዘለቄታው ከተዘፈቀበት የድህነት አዙሪት እንዲወጣ ለማድረግ በመንግስት በኩል ምን አይነት ዘላቂ መፍትሔ እየተሰጠ ይገኛል?” ሲሉም አቶ ፋራህ ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በሶማሌ እና ቦረና አካባቢዎች በአካል ጭምር በመገኘት ችግሩ በትክክልም እንዳለ እንዳረጋገጡ ገልጸዋል። ችግሩን ከአጭር ጊዜ አንጻር ለመፍታት “የዕለት ደራሽ ምግብ ለማድረስ ሙከራ ተደርጓል” ያሉት አብይ፤ 750 ሺህ ገደማ ኩንታል እህል ወደ አካባቢዎቹ መላኩን በምሳሌነት አንስተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሶማሌ እና ቦረና አካባቢዎች በአካል ጭምር በመገኘት ድርቅ በትክክልም እንዳለ እንዳረጋገጡ ገልጸዋል | ፎቶ፦የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

በአካባቢዎቹ የተፈጠረውን የውሃ እጥረት ለማቃለል “259 ቦቴዎች እንዲያጠጡ” መደረጉን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የከብት መኖ ወደ ቦታዎቹ መላኩንም አስረድተዋል። ለህጻናት አልሚ ምግብ እና ክትባቶች መሰጠታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማክሰኞ የፓርላማ ማብራሪያቸው አንስተዋል።

የረዥም ጊዜ መፍትሔ ተደርጎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠቆመው፤ የውሃ አጠቃቀም አስተዳደርን (management) ማሻሻል ነው። “ውሃ! ውሃ! ውሃ! የኢትዮጵያ መፍትሔ እሱ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያቸው ላይ በአጽንኦት ተናግረዋል። 

አርብቶ አደሮች “የገበያ ትስስር በመፍጠር ከብቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን መንገድ መፍጠር” በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛ  መፍትሔነት የተነሳ ነው።  “ለዚያ ምቹ ነገር እየተፈጠረ ከሄደ ቦረናም ሶማሌም በእርግጠኝነት ለሰው ይተርፋሉ። ምርጥ መሬት አላቸው፤ ሰው አላቸው፡፡ ችግሩ ውሃ አድርሰን እያረሱ፤ ከብቶቻቸውንም በተለመደው መንገድ እያረቡ፤ ከሁለቱ እየተጠቀሙ አንዱ ሲጎዳ በአንዱ survive እንዲያደርጉ አለማድረጋችን ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በረዥም ጊዜ መፍትሔነት ከጠቀሷቸው ውስጥ አርብቶ አደሮች “የገበያ ትስስር በመፍጠር ከብቶቻቸውን የሚሸጡባቸውን መንገድ መፍጠር” የሚለው ይገኝበታል | ፎቶ፦ ዩኒሴፍ ኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው መልዕክታቸው ደግሞ “በየአስር ዓመቱ ኢትዮጵያን እየተመላለሰ የሚጎበኝ ነው” ላሉት ድርቅ እና ርሃብ “ዘላቂ መፍትሔ የሚሆኑ ናቸው” ያሏቸውን ሌሎች አካሄዶች አቅርበዋል። ዘላቂ መፍትሔ እንዲያመጡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተጠቀሱ አካላት ውስጥ ባንኮች ይገኙበታል።     

“በአገልግሎት እና ግንባታ ዘርፍ ገንዘብ በማቅረብ ለውጥ እንዳመጡ” በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመሰከረላቸው ባንኮች፤ ለግብርና ዘርፉም ተመሳሳይ ድጋፍ የሚያደርጉበትን መንገድ መቀየስ እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። ከምርጥ ዘር፣ የግብርና ግብዓት እና መሳሪያዎች አቅርቦት ጋር በተገናኘ መስራት የሚፈልጉ አካላት ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ልዩ ልዩ ማበረታቻዎችን እንደሚያዘጋጁላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። 

በሰፋፊ የመስኖ ግብርና ላይ የሚሰማሩ የግል ኢንቨስተሮችም በተለያየ መንገድ እንደሚበረታቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪነት አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው መልዕክታቸው ስለ ማበረታዎች ቢጠቅሱም ዝርዝሩን ከማብራራት ግን ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]