በሃሚድ አወል
ከሶስት ዓመት በፊት የተቋቋሙት የእርቀ ሰላም እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች ንብረት፣ ቢሮ እና በጀት፤ አዲስ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲተላለፍ ተወሰነ። አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ፤ በአዲስ አበባ አሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ በሚገኘው የሁለቱ ኮሚሽኖች ቅጥር ግቢ ውስጥ ቢሮ ማደራጀት መጀመሩን የተቋማቱ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
ከሁለት ወር በፊት በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ በኃላፊነት የሚመሩ 11 ኮሚሽነሮች በተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው የጸደቀው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ነበር። በአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት፤ ኮሚሽኑ የራሱን ጽህፈት ቤት እና ምክር ቤት ያደራጃል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ በመሆን ባለፈው ሳምንት ሰኞ ቃለ መሃላ የፈፀሙት ፕ/ር መስፍን አርአያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ አዲሱ ኮሚሽን ከፌደራል መንግስት ባገኘው ይሁንታ መሰረት ቢሮ የማደራጀት ስራውን ጀምሯል። የምክክር ኮሚሽኑ የሚገለገልባቸውን ቢሮዎች በማደራጀት ላይ የሚገኘው፤ በአዲስ አበባው የአሜሪካ ኤምባሲ አጠገብ በሚገኘው የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲሁም የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን በሚገኙበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ባለበት ቅጥር ግቢ ውስጥ፤ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ስራ ለመጀመር የሚያስችለው ቢሮ እየተዘጋጀለት” እንደሚገኝ የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ሰብለ ኃይሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማረጋገጫ ሰጥተዋል። የፌደራል መንግስት ቅጥር ግቢውን ከመስጠት ባሻገር፤ የሁለቱን ኮሚሽኖች “ንብረት እና ቢሮ” አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ እንዲጠቀመበት እንደፈቀደ የምክክር ኮሚሽኑ ሰብሳቢ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
ፕ/ር መስፍን “እኛ ዝም ብለን መውረስ አንፈልግም። መጀመሪያ ያላቸው ንብረት ኦዲት ተደርጎ ለመንግስት ርክክብ ካደረጉ በኋላ ወደ እኛ እንዲተላለፍ ጠይቀናል” ሲሉ በሁለቱ ኮሚሽኖች እና በአዲሱ ኮሚሽን መካከል የሚደረገውን የርክክብ ሂደት አካሄድ አስረድተዋል። ሁለቱ ኮሚሽኖች ይገለግሉባቸው ከነበሩ ቢሮዎች እና ንብረቶች በተጨማሪ ተመድቦላቸው ከነበረው በጀት ውስጥ የተረፋቸውን ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንዲያስተላለፉ መወሰኑን ተናግረዋል።
የእርቀ ሰላም እና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች ለ2014 በጀት ዓመት የተመደበላቸው 47 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው። ከዚህ 25.7 ሚሊዮን ብሩ የተመደበው ለአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ሲሆን፤ ቀሪው 21.4 ሚሊዮን ብር የተበጀተው ደግሞ ለእርቀ ሰላም ኮሚሽን ነው።

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት አዋጅ ኮሚሽኑ በመንግስት የሚመደብ በጀት እንደሚኖረው ደንግጓል። የምክክር ኮሚሽኑ ስለሚመደብለት በጀት የተጠየቁት ሰብሳቢው፤ “እንደ አስፈላጊነቱ [በጀት] እንጠይቃለን። ስራችንን ሙሉ በሙሉ ስናውቀው ይኼን ያህል ያስፈልገናል እንላለን” ሲሉ ኮሚሽኑ በሁለት እግሩ ከቆመ በኋላ በጀት እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በጀት የማዘጋጀት ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ለኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ነው። የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት፤ ስራውን ለማከናወን የሚያስችሉት “አስፈላጊ ሰራተኞች” እንደሚቀጠሩለት በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ሰፍሯል። የነባሮቹን ኮሚሽኖች ንብረት፣ ቢሮዎችን እና በጀት የሚረከበው የምክክር ኮሚሽኑ፤ የኮሚሽኖቹን “ሰራተኞች አብሮ እንዲረከብ” ንግግር እየተደረገ መሆኑን የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል።
በሁለቱ ኮሚሽኖች ስር ያሉት 40 ገደማ ሰራተኞች “ልምድ ያላቸው ናቸው” የሚሉት ሰብለ፤ “ሰራተኛ መቅጠር አስቸጋሪ ሂደት ነው። ስለዚህ ያ ሁሉ ውስጥ ሳይገባ፤ በቀላሉ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ከአዲሱ ኮሚሽን ጋር እንዲቀጥሉ እየተነጋገርን ነው” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሯ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በ2011 ዓ.ም በአዋጅ የተቋቋሙት የእርቀ ሰላም እና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች በጀት እና ንብረታቸው ወደ አዲሱ ኮሚሽን የሚዘዋወረው፤ የስራ ዘመናቸውን በማጠናቀቃቸው ነው። የኮሚሽኖቹ የሶስት ዓመት የስራ ዘመን የተጠናቀው ከአንድ ወር ገደማ በፊት ነው። የኮሚሽኖቹ የስራ ዘመን “እንደ ሁኔታው” ሊራዘም እንደሚችል በኮሚሽኖቹ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ ቢደነገግም፤ የሁለቱን ኮሚሽኖች ቀጣይነት በተመለከተ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
የእርቀ ሰላም ኮሚሽን የስራ ዘመን ይራዘም እንደው ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ሰብለ ኃይሉ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የስራ ማጠናቀቂያ እና የማጠቃለያ ሪፖርት” እንዲያቀርቡ በደብዳቤ መጠየቃቸውን ተናግረዋል። የተወካዮች ምክር ቤት ለነባሮቹ ኮሚሽኖች ከሁለት ሳምንት በፊት በጻፈው ደብዳቤ፤ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት የአንድ ወር ቀነ ገደብ እንደሰጠ ሰብለ ገልጸዋል።
ሁለቱ ኮሚሽኖች ለፓርላማ በሚያቀርቡት ሪፖርታቸው፤ ከተቋቋሙ ጀምሮ ያከናወኗቸውን ተግባራት፣ ያጋጠሟውን ችግሮች እና ያልተጠናቀቁ ስራዎቻቸውን በዝርዝር ማካተት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል። “ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ [የኮሚሽኖቹ] ስንብት እንዴት መሆን እንዳለበት እና ምን መደረግ አለበት የሚለውን፤ ኮሚሽኖቹ በአንድ ላይ የራሳቸውን አስተያየት እንዲሰጡ እድል ተሰጥቷቸዋል” ሲሉ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በጀት እና ቢሯቸውን ለአዲሱ አገራዊ ምክከር ኮሚሽን የሚያስረክቡት የእርቀ ሰላም እና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች፤ የስራ ዘመናቸው እንዲራዘም ለማድረግ እንቅስቃሴ ላይ ነበሩ። የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ያሉበትን የህግ ክፍተቶችን ለማረም እና የስራ ዘመኑን ለማራዘም የማቋቋሚያ አዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ጀምሮ ነበር።
የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር፤ ማሻሻያ የተደረገበት የአዋጅ ረቂቅ ወደ ፍትህ ሚኒስቴር ከተላከ በኋላ “ወደሚቀጥለው ደረጃ የሄደ አይመስለኝም” ሲሉ ማሻሻያው ተግባራዊ አለመደረጉን አስረድተዋል። የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በአዋጅ ሲቋቋም “ጉልህ የሰብዓዊ መብቶችን ማጣራት፣ ግጭቶችን መፍታት እና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር መስራት” የሚሉ ሶስት ዓላማዎችን ይዞ ነበር።
በተመሳሳይ ወቅት የተቋቋመው የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንም የስራ ዘመኑ ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ተጠናቅቋል። ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያላቸውን ጥናቶች “በጊዜ አጠናቅቆ መጨረስ ባለመቻሉ” የስራ ጊዜው ለተጨማሪ ሶስት ዓመታት እንዲራዘም ጥያቄ ማቅረቡን የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አወል ሁሴን ከሳምንታት በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር።

የአስተዳደር ወሰን እና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ባለፈው ታህሳስ ወር በሰጠው መግለጫ፤ ከሰኔ 2012 ጀምሮ አገር አቀፍ የጥናት እና ምርምር ስራን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል። በመላው ኢትዮጵያ ባሉ 56 ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ለ18 ወራት ሲካሄድ የቆየው አገር አቀፍ ጥናት፤ በአስተዳደር ወሰን፣ በማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር ኮሚሽኑ በወቅቱ ገልጿል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለቤትነት በተመራው እና 28 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተሳትፈውበታል የተባለው ይህ ጥናት “መጨረሻ ደረጃ ላይ” መድረሱንም በታህሳስ ወር መጨረሻ በተሰጠው የኮሚሽኑ መግለጫ ተመላክቷል። በጥናቱ “በርካታ በምክረ-ሀሳብነት ደረጃ ሊቀርቡ የሚችሉ ግኝቶች” መለየታቸውን ኮሚሽኑ በወቅቱ ገልጾ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)