በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሁለት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ስለ አገራዊ ምክክሩ ሂደት ማብራሪያ እንዲሰጡ ውሳኔ አሳለፈ። በጋራ ምክር ቤቱ አባላት ፊት በአካል ቀርበው ማብራሪያ እንዲሰጡ የተባሉት ባለስልጣናት፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ናቸው።
የጋራ ምክር ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 22፤ 2014 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብበት በነበረው የአገራዊ ምክክር ጉዳይ ላይ ለአራተኛ ጊዜ ተወያይቷል። የገዢው የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 50 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በተገኙበት በዛሬው ጉባኤ፤ አገራዊ የምክክር ሂደቱ “የግልጽነት እና አካታችነት ችግር አለበት” የሚሉ አቋሞች በበርካታ ተሳታፊዎች ተንጸባርቀዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በአገራዊ ምክክሩ ሂደቱ ላይ ሙሉ ቀን የፈጀ ውይይት ካካሄዱ በኋላ በጉዳዩ ላይ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤውና የፍትህ ሚኒስትሩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ስለ አገራዊ የምክክር ሂደቱ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ “ምላሽ ሳይሰጡ በዚህ ፍጥነት ለመሄድ የተገደዱበትን ምክንያት፣ የሄዱበትን አካሄድ እና መስፈርቶቻቸውንም በተመለከተ” ከጋራ ምክር ቤቱ ጋር ተገናኝተው እንዲወያዩ የዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ወስኗል።
ባለስልጣናቱ “በተቻለ መጠን እስከ ማክሰኞ እንዲያነጋግሩን ነው የተስማማነው። እኛ እንዲያነጋግሩን በደብዳቤ እንጠይቃቸዋለን። ከተቻለ እስከ ማክሰኞ በአስቸኳይ ቢያደርጉት ጥሩ ነው። አገራችን ካለችበት ሁኔታ እንደገና ደግሞ ቤቱም አስቸኳይ ምላሽ ከመፈለጉ አኳያ በዛ አግባብ ብናይ ብለናል” ሲሉ የጋራ ምክር ቤቱ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንደሚፈልግ ሰብሳቢዋ አብራርተዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው የተገኙት ዶ/ር አለሙ ስሜ፤ ሁለቱ ባለስልጣናት በስም ተጠቅሰው መጠራታቸውን ተቃውመውታል። “የአገራዊ ምክክሩ ሂደቱ ችግር የለበትም የሚል አቋም አለኝ። ግን ‘አልገባንም ግልጽ አይደለም’ የሚሉ አሉ። ያልገባቸውን፤ የሚመለከታቸው አካላት መጥተው ግልጽ ያድርጉ በሚለው ተስማምቻለሁ። አልገባኝም የሚል አካል እስካለ ድረስ ምንም ችግር የለውም” ያሉት ዶ/ር አለሙ፤ ሆኖም “እከሌ ካልመጣ ብሎ ማለት ጥሩ አይደለም” ሲሉ የተቃውሞ አስተያየታቸውን አሰምተዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሉ “ባለቤቱ እኮ ከዚህ በኋላ ኮሚሽነሮቹ ናቸው። ብልጽግናም ባለቤት አይደለም። ብልጽግናም አንድ ተሳታፊ ነው” ሲሉ ማብራሪያ መስጠት የሚገባቸው ባለፈው ሳምንት በተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት አስራ አንዱ ኮሚሽነሮች እንጂ የመንግስት ባለስልጣናት እንዳልሆኑ ተከራክረዋል።
ይህ የዶ/ር አለሙ መከራከሪያ ከኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቃውሞ ገጥሞታል። “በትክክል ያልተመረጠን አካል እውቅና የምንሰጥበት ምክንያት በምን መስፈርት ነው” ሲሉ የጠየቁት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ “አሁን የተመረጠው አካል ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ነው። ስለዚህ ራሱን እንደገና መፈተሽ አለበት” ሲሉ ተችተዋል።
ኦፌኮን ጨምሮ በጠቅላላ ጉባኤው ከተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሰባቱ፤ “ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ውይይት አያስፈልገም” የሚል አቋማቸውን አንጸባርቀዋል። ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ምክክሩ ላይ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች፤ “በመንግስት አካላት አልተደመጠም” የሚል እምነት ያላቸው የፓርቲ ተወካዮቹ፤ “አቋማችንን ይዘን ወደ ህዝብ እንውጣ” የሚል ሀሳብ ሲያራምዱም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአገራዊ ምክክሩ ሂደት ለጊዜው ባለበት ቆሞ በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ ውይይት እንዲደረግበት ከሁለት ሳምንት በፊት በይፋ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ምክር ቤቱ ጥያቄውን ያቀረበው፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት እና ለአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ባስገባው ደብዳቤ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት የአፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላቀረቡት ጥያቄ ይፋዊ ምላሽ ሳይሰጥ፤ ለአገራዊ ኮሚሽን የታጩ ኮሚሽነሮችን በፓርላማ እንዲሾሙ አድርጓል።
“[ባለስልጣናቱ] ካልመጡ፤ እርሱ የእነሱ ድክመት ነው። አለመምጣቱም መልስ ይሆናል፤ መጥተው ቢመልሱ ደግሞ የተሻለ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው ነው የሚወስነው።”
ዶ/ር ራሄል ባፌ- የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤም ሆነ የፍትህ ሚኒስትሩ፤ በፓለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ለቀረበላቸው የማብራሪያ ስጡን ጥያቄ የይሁንታ መልስ ካልሰጡ፤ ቀጣይ ውሳኔያቸው ምን እንደሚሆን ለምክር ቤቱ ሰብሳቢ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ዶ/ር ራሄል፤ “[ባለስልጣናቱ] ካልመጡ፤ እርሱ የእነሱ ድክመት (weakness) ነው። አለመምጣቱም መልስ ይሆናል፤ መጥተው ቢመልሱ ደግሞ የተሻለ ይሆናል። ከዚያ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤው ነው የሚወስነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)