በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ ጥሰቶችን ለሚመረምረው ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ሶስት አባላት ተሾሙ

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት እና ሌሎች ጥሰቶችን ለመመርመር ላቋቋመው ኮሚሽን ሶስት አባላት ሾመ። ኮሚሽኑን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተሾሙት በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከዚህ ቀደም በአቃቤ ህግነት ያገለገሉት ጋምቢያዊቷ ፋቱዋ ቤንሱዳ ናቸው።

በመርማሪ ኮሚሽኑ ውስጥ በአባላነት የተሾሙት ሌሎች የህግ ባለሙያዎች ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እና አሜሪካዊው ስቴቨን ራትነር ናቸው። ሶስቱ የህግ ባለሙያዎች በኮሚሽኑ እንዲያገለግሉ መሾሟቸውን ዛሬ ረቡዕ የካቲት 23 ያስታወቁት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አምባሳደር ፌዴሪኮ ቪሌጋስ ናቸው። 

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የሚባሉ የሰብዓዊ መብት እና ሌሎች ጥሰቶችን ለመመርመር ኮሚሽን ያቋቋመው ታህሳስ 8፤ 2014 በስዊዘርላንድ ጄኔቫ ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ላይ ነበር። የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ ካሉት 47 አባል ሀገራት መካከል አስራ አምስቱ ኮሚሽን የሚያቋቋመውን የውሳኔ ሃሳብ በወቅቱ ተቃውመውት ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)