የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል ተባለ

በሃሚድ አወል

የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ። የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ትላንት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በጋምቤላ የኑዌር እና አኙዋ ዞኖች በፈጸሙት ጥቃት የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቡን ዊው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ የመጀመሪያውን ጥቃቱን የሰነዘሩት በኑዌር ዞን፣ መኮይ ወረዳ፣ ላንግጆክ ቀበሌ መሆኑን የጋምቤላ ፕሬስ ሴክሬተሬያት ጽህፈት ቤት ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በዚህ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል በሌላ ግለሰብ ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። 

ከደቡብ ሱዳን በሚነሱት የሙርሌ ጎሳዎች በጋምቤላ ጥቃት ሲፈጸም ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የትላንቱ ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የሙርሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት በአኙዋ ዞን የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ግለሰቦች ህይወት ማለፉን የሚናገሩት አቶ ቡን፤  ታጣቂዎቹ ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ በተመሳሳይ በፈጸሙት ጥቃት አንድ የክልሉ ፖሊስ አባልን ጨምሮ አስር ሰዎች መገደላቸውን አስታውሰዋል። 

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከሰዎች ግድያ ባለፈ፤ ህጻናትን አግተው እንደሚወስዱ እና ከብቶችን እንደሚዘርፉ አቶ ቡን አብራርተዋል። “[ታግቶ] የተወሰደ ልጅ እንደማይድን ነው የሚቆጠረው” ሲሉ ከክልሉ ታፍነው የሚወሰዱ ህጻናት ደብዛቸው ከእነ አካቴው ጠፍቶ ሊቀር እንደሚችል አመልክተዋል። 

ታጣቂዎቹ በጋምቤላ ተጠልለው በሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ ጭምር ተመሳሳይ የህጻናት እገታ እንደሚፈጽሙ ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። በመገባደድ ላይ ባለው የካቲት ወር መጀመሪያ፤ በጋምቤላ ክልል አኙዋ ዞን ዲማ ወረዳ በሚገኘው ኡኩቡ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ የሙርሌ ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው አምስት ህጻናትን አግተው መውሰዳቸውን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት አስታውቆ ነበር። 

የሙርሌ ጎሳዎች በጋምቤላ የአኙዋ እና ኑዌር ዞኖች የሚያደርሱት ጥቃት ከክልሉ “ከክልሉ አቅም በላይ እየሆነ” መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ቡን ዊው፤   ጥቃቶቹን ለመከላከል የፌደራል መንግስት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባው አሳስበዋል። በታጣቂዎቹ የሚፈጸመውን ይህን መሰል ጥቃት የፌደራል መንግስት በዘላቂነት ለምን መፍታት እንዳልቻለ በፓርላማ ጭምር ጥያቄ አስነስቶ ነበር። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 15 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ይህን ጥያቄ ያነሱት ከጋምቤላ ማጃንግ ዞን ተወክለው ፓርላማውን የተቀላቀሉት አቶ አሽኔ አስቲን ናቸው። የጋምቤላ ክልል ታጣቂዎች በሚሰነዝሩት ጥቃት ምክንያት “የተረጋጋ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ እስከ አሁን መግባት አልቻለም” ያሉት አቶ አሽኔ፤ “አሁንም የሰው ህይወት እያለፈ ይገኛል፤ ህጻናትም እየተሰረቁ ነው” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አስረድተዋል።

የፓርላማ አባሉ አስከትለውን “ይህንን ድንበር ዘለል የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ለምን ጥረት አልተደረገም?” የሚል ጥያቄ በተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ ለመስጠት ለተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሰንዝረዋል። “የሙርሌ እና ቡሜ ጎሳዎች [ጥቃት] ትክክለኛ ችግር ነው” ሲሉ በጋምቤላ ክልል ችግር መኖሩን ያመኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ነገሩን በውይይት ለመፍታት እየጣረ መሆኑን አስረድተዋል። 

ሁለቱ ጎሳዎች ከኢትዮጵያ ጋር በሚጎራበቱ የደቡብ ሱዳን ቦታዎች እንዳሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እንግዲህ ጎረቤት ስንሆን ጸጋም፣ መከራም መጋራት ነው። ባህል ነው። እነዚያን ብሄረሰቦች ልናጠፋቸው አንችልም፤ ጎረቤቶች ናቸው” ብለዋል። በጋምቤላ ክልል በተደጋጋሚ በሚፈጸሙት ጥቃቶች “እነሱም ተፈትነዋል፤ እኛም ተፈትነናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ችግሩ “ወደ ፊት እያየን የሚፈታ ይሆናል” ሲሉ ለፓርላማ አባሉ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

በጋምቤላ ክልል ያለውን ይህን ችግር ለመቅረፍ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራ ልዑክ ወደ ደቡብ ሱዳን አቅንቶ እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል። የጋምቤላ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችን ያካተተው ልዑክ ወደ ደቡብ ሱዳን ያቀናው ከአንድ ወር በፊት ጥር 24፤ 2014 ነበር።

የልዑኩ አባላት ከደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዳት ጋር በዋናነት የተወያየው “በኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን አዋሳኝ ክልሎች አካባቢ ባለው የጸጥታ ሁኔታ” ላይ እንደሆነ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። በውይይቱ ወቅት ከተነሱት የጸጥታ ጉዳዮች ውስጥ “የህጻናት ጠለፋ ወንጀሎች እና የቁም እንስሳት ዝርፊያ” ችግሮች እንደሚገኙባቸው ምክር ቤቱ መግለጹ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)