የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዩክሬን ጉዳይ ላይ በጠራው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ኢትዮጵያ ድምጽ ሳትሰጥ ቀረች

ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ጦርነት ለማውገዝ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ኢትዮጵያ ድምጽ ሳትሰጥ ቀረች። ከ40 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ሩሲያን የሚያወግዝ የውሳኔ ሀሳብ ዛሬ ረቡዕ አጽድቋል። 

በዚህ የተመድ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 13 አገራት ጭርሱን ድምጽ ሳይሰጡ ቀርተዋል። ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችውን ዘመቻ እንድታቆም እና ጦሯን ሙሉ በሙሉ እንድታስወጣ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሀሳብ 141 አገሮች ሲደግፉት፤ ኤርትራን ጨምሮ አምስት አገሮች ተቃውመውታል። 

የውሳኔ ሃሳቡ በቀጥታ የሚመለከታት ሩሲያ እና ለሩሲያ ጦር በመሸጋገሪያነት እያገለገለች ያለችው ቤላሩስ የውሳኔ ሀሳቡን ከተቃወሙ ውስጥ ይገኙበታል። በሀገሯ ለዓመታት በቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት ከሩሲያ ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ስታገኝ የቆየችው ሶርያ እና አሜሪካ ሁሌም በአይነ ቁራኛ የምትከታተላት ሰሜን ኮሪያ የውሳኔ ሀሳቡ የተቃወሙ ሌሎች ሀገራት ናቸው። 

በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ 35 አገራት ድምጸ ተአቅቦ አድርገዋል። ከአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ የውሳኔ ሀሳቡን የደገፉ ሲሆን ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በአንጻሩ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል። ድምጽ ሳይሰጡ ከቀሩ አገሮች መካከል ስምንቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ጭርሱን ድምጽ ካልሰጡት ውስጥ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ቶጎ ይገኙበታል።  

በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ድምጽ ሳይሰጡ መቅረት አገራት በጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋም የሚያሳዩበት አንድ መንገድ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከዲፕሎማቲክ ምንጮች ለመረዳት ችላለች። አብዛኞቹ ድምጽ ያልሰጡ አገሮች ተወካዮች በስብሰባ አዳራሹ ቢገኙም የድምጽ መስጫ ቁልፉን ሳይጫኑ ሊቀሩ አሊያም ድምጽ መስጠት ሲጀመር ጥለው ሊወጡ እንደሚችሉ የስብሰባውን አካሄድ የሚያውቁ ይናገራሉ። 

የአገራቱ ድምጽ አለመስጠት በይፋ ባይቆጠርም የራሱን ፖለቲካዊ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ የዲፕሎማቲክ ምንጮች ይናገራሉ። “የዚህ ትርጉም ከነገሩ የለሁበትም እንደማለት ነው። በድምጽ መስጠቱ መሳተፍ አለመፈለግን የሚያሳይ ነው” ሲሉ አንድ የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በሩሲያ ላይ ዛሬ ያጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ አስገዳጅ ባይሆንም፤ አለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት ያንጸባረቀበት ነው። ከ100 በላይ አገራት በትብብር ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ የሩሲያን “ጥቃት” የኮነነ ሲሆን ሀገሪቱ ጦሯን አለም አቀፍ እውቅና ከተሰጠው የዩክሬን ድንበር እንድታስወጣም ጠይቋል። ከዚህ በተጨማሪም የፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መንግስት ለዩክሬን ሁለት ተገንጣይ ግዛቶች የሰጠውን እውቅናም እንዲያጥፍም ጥያቄ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)