የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ ቻይና ጥሪ አቀረበች

የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) “ልዩነቶቻቸውን በውይይት እና በድርድር እንዲፈቱ” ቻይና ጥሪ አቀረበች። በቅርቡ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ልዩ ልዑክ የሾመችው፤ ቻይና በጉዳዩ ላይ “ንቁ እና ገንቢ ሚና ለመጫወት” ዝግጁ መሆኗንም አስታውቃለች።

ቻይና ይህን ያለችው በሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን አማካኝነት ዛሬ ሐሙስ የካቲት 24 ባስተላለፈችው መልዕክት ነው። ቃል አቃባዩ በመስሪያ ቤታቸው የተረጋገጠ የፌስቡክ ገጽ ባሰፈሩት አጭር መልዕክታቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ የሚያደርገውን ግስጋሴ ለማቆም መወሰኑ እና በአገሪቱ ተደንግጎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀድሞ እንዲነሳ ማድረጉን ቻይና እንደታዘበች ጠቅሰዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት ለአካታች አገር አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት ሲዘጋጅ መቆየቱ “በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማርገብ አዎንታዊ ጠቀሜታ” እንደሚኖረው ዋንግ ዌንቢን አንስተዋል። ቻይና “እንደ ቅን የኢትዮጵያ ወዳጅ” ጦርነቱ በውይይት እና በድርድር እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላት የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በዛሬ መልዕክታቸው ይፋ አድርገዋል። 

“የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ልዩነቶቻቸውን በውይይት እና በድርድር ለመፍታት እና አገሪቱን ወደ ሰላም፣ ልማት እና መነቃቃት ጎዳና ለመመለስ በጋራ እንዲሰሩ ቻይና ጥሪ ታቀርባለች” ሲሉም ዋንግ ዌንቢን የሀገራቸውን አቋም አንጸባርቀዋል። “በዚህ ረገድ ንቁ እና ገንቢ ሚናችንን ለመጫወት ዝግጁ ነን” በማለትም ቻይና ለጉዳዩ የሰጠችውን ትኩረት የሚጠቁም አስተያየት አክለዋል። 

ቻይና፤ አለመረጋጋት ለጠናበት የአፍሪካ ቀንድ ባለፈው የካቲት አጋማሽ ልዩ ልዑክ በመሾም፤ የአፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካ እና ፈረንሳይን መንገድ ተከትላለች። ከዚህ ቀደም በፓፕዋ ኒው ጊኒ በአምባሳደርነት የሰሩት ሸዌ ቢንግ የተባሉት የቻይና ልዩ ልዑክ፤ በአፍሪካ፣ ኦሺኒያ እና አሜሪካ ተዘዋወረው መስራታቸውንም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ተሿሚው ዲፕሎማት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ባሉ ሀገራት ቻይና ማየት የምትፈልገውን “ሰላም የሰፈነበት ዕድገት” የማሳደግ ሚና ይወጣሉ ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)