በሃሚድ አወል
መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ከተሳነው ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ፈጥሮ እንደሚታገል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አስታወቀ። በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው “ኦነግ ሸኔ” ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ መንግስት ባለስልጣን ድረስ “የሰርጎ ገብ አደረጃጀት አለው” ሲል የወነጀለው ፓርቲው፤ መንግስት የህዝብ ደህንነት እንዲያስጠብቅ እና መዋቅሩን “በጥልቀት” እንዲፈትሽ አሳስቧል።
ኢዜማ ማሳሰቢያውን የሰጠው ዛሬ አርብ የካቲት 25፤ 2014 በአዲስ አበባ ስቴዲየም አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የዛሬው የኢዜማ መግለጫው ትኩረት ካደረገባቸው አምስት ነጥቦች አራቱ በጸጥታ እና ግጭት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
በኦሮሚያ ክልል ያለውን የጸጥታ ሁኔታ የዳሰሰው የኢዜማ መግለጫ አንዱ ክፍል፤ በክልሉ በተደጋጋሚ “ጥፋት” እየፈጸመ ይገኛል ያለውን “የኦነግ ሸኔን” ቡድን የተመለከተ ነው። በኢዜማ መግለጫ “የሽብር ቡድን” በሚል የተጠራው “ኦነግ ሸኔ”፤ በመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ድጋፍ በማግኘት አላማውን በማስፈጸም ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ኦነግ ሸኔ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በአንድ ለአምስት አደረጃጀት የኢኮኖሚ እና ቁሳቁስ ድጋፍ የሚያመቻች “ምስጢራዊ ቡድን አዋቅሯል” ሲል ኢዜማ በዛሬው መግለጫው ወንጅሏል። “የሽብር ቡድኑ” ከተራ አባል አንስቶ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ድረስ “የሰርጎ ገብ አደረጃጀት” አለው ሲል የሚከስሰው ኢዜማ፤ ቡድኑ ባደራጀው ምስጢራዊ ቡድን መረጃዎችን ያገኛል ባይ ነው።
ኢዜማ በመግለጫው ያነሳው ሌላኛው ከጸጥታ ጋር የተያያዘ ጉዳይ፤ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሳቢያ የተፈጠሩ ችግሮችን ናቸው። በአማራ ክልል ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ልዑክ መላኩን ያስታወሰው ፓርቲው፤ በደቡብ እና እና ሰሜን ወሎ ዞን ደረሱ ያላቸውን ችግሮች በመግለጫው ዘርዝሯል። በአማራ ክልል “ሕገ ወጥ የመሳሪያ ንግድ እና ዝውውር እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያለው ኢዜማ፤ “አንዳንድ ከተሞች ከፍተኛ የጦር መሳሪያ መሸጫ ማዕከል እየሆኑ መጥተዋል” ብሏል።
የህወሓት ኃይሎች ከአማራ ክልል መውጣትን ተከትሎ፤ “ሸሽተው የነበሩ የብልጽግና አመራሮች” ወደ ክልሉ ተመልሰው ማስተዳደር ከጀመሩ በኋላ “በርካታ አዳዲስ የታጠቁ ቡድኖች፣ ሃይማኖት ተኮር የወጣት ሊጎች የመሳሰሉ አደረጃጀቶች” መፈጠራቸውን ኢዜማ ገልጿል። ኢዜማ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አሉ ያላቸውን “ችግሮች ለማስወገድ እና በጋራ ለመስራት” የሁለቱን ክልሎች ርዕሳነ መስተዳደሮች ለማነጋገር በደብዳቤ ቢጠይቅም ፍቃደኛ አለመሆናቸውን አስታውቋል።
ኢዜማ በመግለጫው ያነሳው ሶስተኛው ነጥብ በአፋር ክልል በህወሓት ቁጥጥር ስር ያሉትን አካባቢዎች የሚመለከት ጉዳይ ነው። ፓርቲው “የህወሓት ጦር ከአፋር ክልል ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ እስኪወጣ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ተቀዳሚ ስራው የሆነው መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ” ሲል አሳስቧል።
“የህወሓት ጦር ሙሉ በሙሉ ከአፋር እና አማራ ክልል ባልወጣበት ሁኔታ” መንግስት “የህልውና ዘመቻውን አንደኛውን ምዕራፍ አጠናቅቄያለሁ” ማለቱን፤ ኢዜማ “ግብታዊ ውሳኔ” ሲል ነቅፎታል። በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉም “ጦርነቱ ሳያልቅ፤ ጦሱን አማራ እና አፋር ክልል ላይ ጥለን፤ አልቋል ብለን መሄድ ተገቢ አይደለም። ገና እኮ ነው፤ ዋጋ እየተከፈለ ነው ያለው” ሲሉ የፓርቲያቸውን ሃሳብ አንጸባርቀዋል።
አዜማ በመግለጫው ያካተተው ሌላኛው ነጥብ “በመንግስታዊ መዋቅር የታገዙ” ያላቸውን የደቡብ ክልል ግጭቶች ነው። “በደቡብ ክልል የተወሰኑ አካባቢዎች መንግስት ከዚህ ቀደም የወሰደው ልል የህግ ማስከበር ሂደት ቀጠናውን የስጋት ውጥረት እንዲያጠላበት አድርጎታል” ያለው ኢዜማ፤ በክልሉ አለ ላለው “ግጭት” መንግስትን ተጠያቂ አድርጓል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ መቀመጫ ያለው ኢዜማ፤ በዛሬው መግለጫው ለጠቀሳቸው የጸጥታ ችግሮች “የመንግስት መዋቅር በተለያየ ስውር አላማ ባላቸው አካላት መጠለፍ፣ ቀሪውም መዋቅር የህዝብን ጥቅም ለማስከበር አቅሙን አጠናክሮ መስራት አለመቻሉን” በምክንያትነት አንስቷል። የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋም ችግሩ ያለው አሰራር ላይ መሆኑን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
“የአሰራር፣ የፖሊሲ፣ የእዝንላልነት፣ የቸልተኝነት ወይም ስልጣንን የማስቀደም ካልሆነ በስተቀር፤ ሀገሪቷ ውስጥ የመንግስትን የጸጥታ ኃይል ሊገዳደር የሚችል ምንም አይነት ኃይል የለም። እዚህ ሀገር በጣም በርካታ የፌደራል ፖሊስ፤ መከላከያ ነው ያለው። በጣም ብዙ የጸጥታ ኃይል ነው ያለው። የአደረጃጀት እና ለጉዳዩ ትኩረት ያለመስጠት ችግር ነው ብለን ነው የምናምነው” ሲሉ አቶ የሺዋስ ገልጸዋል።
መንግስት ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት በዚሁ ከቀጠለ ግን፤ ኢዜማ ሀገር አቀፍ ወደ ሆነ ትግል መግባቱ እንደማይቀር በዛሬው መግለጫው ጠቁሟል። “መንግስት የዜጎችን የሰቆቃ ድምጽና ዋይታ ችላ በማለት የስልጣን ዘመኑን ለማስጠበቅ ብቻ የሚተጋ እና ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ ከተሳነው፤ ኢዜማ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ በመፍጠር የህዝቡ ወጥቶ መግባት፣ ሁሉም ዜጋ በየትኛውም ስፍራ የመንቀሳቀስ መብቱ እንዲከበር ከፍተኛ ትግል ያደርጋል” ሲል ፓርቲው አስታውቋል።
ኢዜማ “ህዝባዊ ንቅናቄ አደርግበታለሁ ያለው ለአረንጓዴ ልማት አይደለም” ያሉት የፓርቲው ሊቀመንበር፤ “ህዝብን በሰላም ወጥቶ መግባትን በሚያረጋግጥ መልኩ [የሚደረግ] ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። በዛሬው የኢዜማ መግለጫው ከጸጥታ ጋር ያልተያያዘ በብቸኝነት የተነሳው ጉዳይ፤ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን እና በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ ነው። ድርቁ በህዝቡ እና በመንግስት ተገቢውን ትኩረት አላገኘም ያለው ፓርቲው፤ “ድርቁን ተረባርቦ ለመመከት በሚደረገው ጥረት ከክልሎች እና ከፌደራል መንግስት የሚቀርብለትን ጥሪ ተቀብሎ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑኑን” አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)